በሆሳዕና ከተማ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የልማት ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ነው

ሆሳዕና፣ መጋቢት 26/2015 (ኢዜአ)፦ በሆሳዕና ከተማ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ግንባታቸው እየተካሄደ ያሉት ፕሮጀክቶች የከተማዋን እድገት ከማመላከት ባለፈ የነዋሪዎቿን ጥያቄዎች የሚመልሱና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው።


 

ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ የከተማውን ገጽታ በመቀየር ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ የነዋሪዎችን ፍላጎትና ተጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ በከተማው አስተዳደርና በህብረተሰቡ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም መልካም በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ።


 

በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተካሄዱ ያሉት ፕሮጀክቶች የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ፣ የአስፋልት መንገድ ሥራና ደረጃ ማሳደግ፣ የድንጋይ ንጣፍና የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ እንደሚያካትቱ ከንቲባው አስረድተዋል።

የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው የመቶ አለቃ ሰብለወርቅ ለማ ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረው መንገድ አመቺነት እንዳልነበረው አስታውሰዋል።


 

የከተማውና አካባቢዋ ነዋሪዎች በተለይ በክረምት ወቅት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሲጋለጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በያዘው አቅጣጫ መሰረት የሚካሄዱት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድጉ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም