ቀጥታ፡

ባለፉት ሰባት ወራት ከ 190ሺህ ዩኒት በላይ ደም ተሰብስቧል - የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2015(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሰባት ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ190ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባና በክልሎች በሚገኙ የደም ልገሳ ክለቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች የደም ልገሳ ክበቦችን በማቋቋም የተማሪዎችን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ መሰራቱንም እንዲሁ።

በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ከ190ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።


 

የተሰበሰበው የደም መጠን ከዕቅዱ አንፃር 77 በመቶ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ለአፈጻጸሙ መቀነስ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግርና የኅብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። 

ተከታታይ የፆም ወቅቶች መምጣታቸውን ተከትሎ የለጋሾች ቁጥር እንዳይቀንስም አገልግሎቱ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራቶች በእቅድ የተያዘውን የደም መጠን ከለጋሾች ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ለረዥም ዓመታትና ለተከታታይ ጊዜ ደም የለገሱ በጎ ፈቃደኞችን እውቅና ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ ለጋሾችን በማበረታታት  ቁጥራቸውን ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ እየተቀረጸ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም