በሚያዝያ ወር ከቀደሙት ሁለት የበልግ ወቅቶች የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በሚያዝያ ወር ከቀደሙት ሁለት የበልግ ወቅቶች የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ መጋቢት 26/2015 (ኢዜአ) በሚያዝያ ወር ከቀደሙት ሁለት የበልግ ወቅቶች የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በሚኖረው ከባድ ዝናብ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በበርካታ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በመጠንም ሆነ በስርጭት የተሻለ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ይኖራል ብሏል።
በመሆኑም በመጪው ሚያዝያ ወር ከቀደሙት ሁለት የበልግ ወራት የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር አስታውቋል።
ከመጋቢት ወር መግቢያ ጀምሮ ለተዘሩ ቡቃያዎችና በተለያየ እድገት ላይ ለሚገኙ አዝመራዎች እንዲሁም ቋሚ ተክሎች ተስማሚ የአየር ጸባይ እንደሚኖር ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።
የሚያዝያ ወር የአየር ጸባይ በሀገሪቱ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ፣ በደጋማው አካባቢ በሚዘሩ ሰብሎችም ሆነ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ለእንስሳት የግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።
እንዲሁ በተለያዩ ምክንያቶች የበልግ ወቅት እርሻ ዘግይተው ለጀመሩና የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት ለሚጠባበቁ አርሶ አደሮች አመቺ የሆነ የአየር ሁኔታ ሰለሚኖር ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ከበልግ ወቅት ዝናብ የመዋዥቅ ባህሪ አንጻር ተከታታይ ደረቃማ ቀናት በወሩ ውስጥ ሊከሰት እንደሚችል የተነበየው ኢንስቲትዩቱ እርጥበት አጠር የሆኑ አካባቢዎች የዝናብ ውሃን የማሰባሰብ ስራ በትኩረት ሊያከናውኑ እንደሚገባም ገልጿል።
በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና በደቡብ የሀገሩቱ ክፍሎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በትንበያው ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊፈጠር ስለሚችል ጎርፍን አስቀድሞ መከላከል ላይ ከወዲሁ የወሃ መፋሰሻዎችን ማጽዳትና ማስተካካል እንደሚገባም ጠቁሟል።
በተከታታይ በሚፈጠር እርጥበት በማሳ ውስጥ ውሃ እንዳይተኛ ለማስወገድ የሚያስችሉ ዘዴዎች ከወዲሁ እንዲተገበሩ መክሯል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ ግድቦች፣ ወንዞች እንዲሁም ሌሎች የውሃ አካላት የተሻለ የውሃ መጠን እንዲያገኙ የሚያስችል ወቅት መሆኑን ጠቁሟል።
በተለይም አብዛኛው የኦሞ ጊቤ ስምጥ ሸለቆ፣ አባይ፣ አዋሽ፣ የታችኛውና የመካከለኛው ተከዜ እንዲሁም የላይኛውና የመካከለኛው አፋር ደናክል እና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ እርጥበት ይጠበቃል።