መንግስት እያደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ የረድኤት ድርጅቶች እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት እያደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ የረድኤት ድርጅቶች እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ መጋቢት 26/2015 (ኢዜአ):- መንግስት ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ እያደረጋቸው የሚገኙ ጥረቶችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትና ለጋሾች እንዲደግፉ ጥሪ አቀረበ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመድ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪና ሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ካትሪን ሶዚ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
መንግስት ከተመድና በስሩ ካሉ ኤጄንሲዎች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
ከሰላም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ መንግስት ብሔራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕ፣ ብሔራዊ እርቅና በተጎዱ አካባቢዎች የተሃድሶ እና የመልሶ ግንባታ ለማካሄድ ያለው ቁርጠኝነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
የተመድ ኤጄንሲዎችና ለጋሾች መንግስት እያደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደግፉ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመድ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪና ሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ካትሪን ሶዚ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ሂደትን ማጠናከሩ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ "የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሁሉንም ያስገረመ ነው” ሲሉ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።