ከዳባት-አጅሬ-ቅራቅር-ከተማ ንጉስ እየተገነባ ያለውን የአስፋልት መንገድ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከዳባት-አጅሬ-ቅራቅር-ከተማ ንጉስ እየተገነባ ያለውን የአስፋልት መንገድ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ ነው
ደባርቅ መጋቢት 26/2015(ኢዜአ)፦ ከ2 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለውን ከዳባት-አጅሬ-ቅራቅር-ከተማ ንጉስ የአስፋልት መንገድ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ብሩክ አዳነ እንደገለጹት፣ 100 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ የሰሜንና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖችን የሚያገናኝ ነው ።
በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ግንባታው ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢንጂነር ብሩክ እንዳሉት በምዕራፍ አንድ ከዳባት-አጅሬ እየተገነባ ያለው የ43 ኪሎ ሜትር ግንባታ አፈጻጸም ከ88 በመቶ በላይ ደርሷል።
ከመንገዱ 22 ኪሎ ሜትር ለሚሆነው አስፓልት የማልበስ ሥራ የተሰራ ሲሆን ለቀሪው ደግሞ የውሀ መሄጃ ትቦ፣ ድልድይ፣ የደጋፊ ግንብ እንዲሁም የመሬት ቆረጣና የአፈር ሙሌት ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
ከዳባት-አጅሬ እየተሰራ ያለው መንገድ በተያዘው ዓመት መጨረሻ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃትም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
"በምዕራፍ ሁለት ከአጅሬ-ቅራቅር-ከተማ ንጉስ እየተገነባ ያለው መንገድ አፈጻጸም ከ62 በመቶ በላይ ደርሷል" ያሉት ኢንጂነር ብሩክ፣ በመጪው ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
መንገዱ በወረዳ ከተሞች 21 ሜትር፣ በቀበሌ ከተሞች 11 ነጥብ 5 እንዲሁም በገጠር የዘጠኝ ሜትር ስፋት ይኖረዋል።
ከዳባት-አጅሬ የሚገነባው የምዕራፍ አንድ መንገድ ፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ተውህቦ ምህረት በበኩላቸው፣ መንገዱ 43 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍንና በጥራት እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በህዝብ ጥያቄ መንገዱን ወደ አስፓልት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለያየ የሙያ መስክ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አመልክተዋል።
የመንገዱን ግንባታ እያከናወነ ያለው የፓወርኮን ኮንስትራክሽን የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዲስ ሙሉነህ በበኩላቸው በምዕራፍ ሁለት እየተገነባ ላለው ከአጅሬ-ቅራቅር-ከተማ ንጉስ መንገድ የመሬት ቆረጣና የአፈር ሙሊት ሥራ በመከናወን ላይ ነው።
ከእዚህ በተጨማሪ የውሃ ማፋሰሻ፣ ደጋፊ ግንብ እና ድልድዮችን በመገንባት አስፋልት ለማንጠፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
"መንገዱ ከመሰራቱ በፊት ሰው ሲታመምና ወላድ እናቶች በምጥ ሲያዙ ወደ ጤና ተቋም ለመውሰድ በእንጨት ተሸክመን ከግማሽ ቀን በላይ እንጓዝ ነበር" ያሉት ደግሞ በሰሜን ጎንደር ዞን የዳባት ወረዳ ነዋሪ አቶ ዘርፉ ታረቀኝ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው መንገድ በመገንባቱ የታመሙና ወላድ እናቶችን በአምቡላንስ እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ፈጥነው ወደ ሃኪም ቤት ለማድረስ መቻላቸውን ገልጸዋል።
"መንግስት የመንገድ ችግራችንን አይቶ መንገድ በመስራቱ የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄያችን ተፈቷል፤ በእዚህም መንግስትን ማመስገን እወዳለሁ" ብለዋል።