የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2015(ኢዜአ)፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ።
የረቂቅ አዋጁን መሻሻል አስፈላጊነት በተመለከተ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ማብራሪያ አቅርበዋል።
በስራ ላይ የነበረው አዋጅ 30 ዓመታትን ያስቆጠረና ለድርጅቶቹ የቦርድ አባላት የተሟላ መብትን የማያጎናጽፍ፣ ተጠያቂነትን የማያረጋግጥ፣ የተሟላ ማዕከላዊ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓትን በአግባቡ ያልዘረጋ እንደነበር አብራርተዋል።
በተጨማሪም በመንግስት በተያዙና በግል ድርጅቶች መካከል ገለልተኝነትን የጠበቀ ውድድር እንዲኖር የማያደርግና ከዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓት ጋር የማይጣጣም መሆኑ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተብራርቷል።
በመሆኑም ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 20/2015 ሆኖ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጠናከር፣ ትርፋማነታቸውን ለማሳደግ፣ ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋትና ተግባራዊ ለማድረግ አዋጁን ለማሻሻል ማስፈለጉ ተገልጿል።
ምክር ቤቱም በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ላይ በዝርዝር ተወያይቶበታል።
በመጨረሻም ከምክር ቤት አባላት የተነሱ አስተያየቶችን ታሳቢ በማድረግ፤ ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።