በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ-ግበር ወልቂጤ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ-ግበር ወልቂጤ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ይጫወታሉ
አዲስ አበባ መጋቢት 26/2015 (ኢዜአ):- በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በወልቂጤ ከተማና ባህር ዳር ከተማ መካከል ይደረጋል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው ወልቂጤ ከተማ በሊጉ እስካሁን 16 ጨዋታዎችን አድርጎ አምስት ጊዜ አሸንፎ፤ አምስት ጊዜ ተሸንፎ፤ ስድስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ16ቱ ጨዋታዎች 20 ግብ አስቆጥሮ 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል። በ21 ነጥብ እና በአንድ የግብ ክፍያ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ወልቂጤ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በአንጻሩ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።
እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች ስምንት ጊዜ አሸንፎ፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ ሽንፈት በማስተናገድ ስድስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
23 ግብ አስቆጥሮ 12 ግቦችን አስተናግዷል። 30 ነጥቦችን በመሰብሰብ እና በ11 የግብ ክፍያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባህር ዳር ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ፌዴራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በተያያዘም ትናንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን አርባ ምንጭ ከተማን እንዲሁም ለገጣፎ ለገዳዲ ድሬዳዋ ከተማን በተመሳሳይ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።