በቄለም ወለጋ ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በቄለም ወለጋ ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ
ጊምቢ መጋቢት 26/2015 (ኢዜአ) በቄለም ወለጋ ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለፀ፡፡
የቄለም ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ ጉርሜሳ እንዳሉት በዞኑ በበጀት ዓመቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ መልክ 13 ሚሊዮን ብር ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብ ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት በተደረገ ርብርብ 19 ሚሊዮን 167 ሺሕ 163 ብር በቦንድ ሽያጭ፤ 100 ሺህ ብር ደግሞ በስጦታ፤ በአጠቃላይ 19 ሚሊየን 267 ሺህ 163 ብር ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
አክለውም የዞኑ ነዋሪዎች የግድቡ መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠ ግዜ ጀምሮ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በህዝቡ ተሳትፎ እየተሰራ ያለ ፕሮጀክት ነው ያሉት አቶ ገመቹ፤ ለዚህም የዞኑ ነዋሪዎች ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ድንጋይ የተጣለበት 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
በዚህ የንቅናቄ መርሃ ግብር ላይ የዞኑ ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ድጋፍ ካደረጉ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሽብሩ ነገራ በሰጡት አስተያየት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
አቶ ሳንበቶ ዋቅጅራ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ ልጆች ላብ እየተሰራ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በዓመቱ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ሲያደረጉ እንደነበር ተናግረው፤ እስከ ፍጻሜው ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡