ቀጥታ፡

የቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሻሻል የመስህብ ልማት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል - የቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2015 (ኢዜአ) የቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሻሻል የመስህብ ልማት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም የቱሪዝም ዘርፉ በሚፈለገው አግባብ ኢኮኖሚውን እየደገፈ አለመሆኑ ይገለጻል፡፡

ከዚህ አኳያ መንግስት የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ዘርፉን ለማነቃቃት እየሰራ ሲሆን፤ ለአብነትም "በገበታ ለሸገር" እና "ገበታ ለሀገር " ፕሮጀክት አማካኝነት የተከናወኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት ስራ ተጠቃሽ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ ባደረጉት "ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት አማካኝነት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ ስምንት የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች የሚለሙ ይሆናል፡፡

በፕሮጀክቱ ከሚለሙት ስምንቱ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች መካከል ሁለቱ በግል ባለሃብቶች እንደሚለሙም ነው የተጠቆመው፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት አምስት ዓመታት የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል፡፡

ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሻሻል የመዳረሻ ስፍራ ልማት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ምቹ ለማድረግ በሚደረገው የልማትና የማስተዋወቅ ስራ በርካታ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል ባለቤት እየሆኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ኢትዮጵያ በሚገባት ልክ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት፡፡ 

በሌላ መልኩ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ እየተነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ኢትዮጵያ ከ500 ሺህ በላይ የውጭ አገር ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም