ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ስራቸውን በ'ንግድ ስራ እቅድ' መምራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ስራቸውን በ'ንግድ ስራ እቅድ' መምራት አለባቸው
አዳማ መጋቢት 25/2015 (ኢዜአ)፡- ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩበት የስራ መስክ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ስራቸውን በ'ንግድ ስራ እቅድ' መምራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
አዋጭነት ባለው የንግድ ስራ እቅድ ወይም 'ቢዝነስ ፕላን' አዘገጃጀት ላይ ያተኮረና ከክልሎችና ከተሞች የተወጣጡ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች በተሳተፉበት የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ አባገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቡዱልፈታህ ያሲን እንደገለፁት ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩበት የስራ መስክ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ስራቸውን በንግድ እቅድ መምራት አለባቸው።
በተለመደውና ኋላ ቀር በሆነ የንግድ አሰራር የሚመሩ ኢንተርፕራይዞች በሚፈለገው ልክ ለውጥ ማምጣት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ይህም በመሆኑ ኢንተርፕራይዞች በአዋጭ የንግድ ስራ እቅድ ወይም 'ቢዝነስ ፕላን' ዝግጅት ላይ ያለባቸውን ክፍተት በአቅም ግንባታ ስልጠና ለመሙላት ኢንስቲትዩቱ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገሪቷ የስራ አጥነትን ለመቀነስ ኢንተርፕራይዞችን በስፋት የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ውጤታማ እንዲሆኑም በአዋጭ የንግድ ስራ ዘርፍ መሰማራት አለባቸው ብለዋል።
የመድረኩ ዓላማም ኢንተርፕራይዞች ያለባቸው አዋጭ የንግድ ስራ እቅድ ዝግጅት ክፍተትን በመሙላት በርካታ ወጣቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማስቻል ነው ብለዋል።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ከውጪ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት አኳያም ትልቅ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
''ከ90 በመቶ በላይ የስራ ዕድል የተፈጠረው በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ነው'' ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለውጤታማነታቸው በዕውቀት ላይ ተመስርተው አዋጭ የስራ ዘርፍ ላይ መሰማራት አለባቸው ብለዋል።
መንግስት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም 38 አይነት ምርቶችን ከውጭ እንዳይገቡ ማድረጉን በማሳያነት አንስተዋል።
እነዚህን ምርቶች ኢንተርፕራይዞች በአገር ውስጥ እንዲያመርቱ በማድረግ የገበያ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማስቻሉንም አቶ አብዱልፈታህ ገልፀዋል።
ኢንተርፕራይዞች የመስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲያገኙ እንዲሁም የብድር አገልግሎት ተደራሽ እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል።
በዚህም ለማሽነሪ ሊዝና ለስራ ማስኬጃ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱን የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑት ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በስልጠናው ላይ ከክልሎች የተወጣጡ 270 ሰልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል ።