የ4 ሺህ ግለሰቦችን አቤቱታ በመመርመር ችግራቸው እንዲፈታ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ ተችሏል- የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
የ4 ሺህ ግለሰቦችን አቤቱታ በመመርመር ችግራቸው እንዲፈታ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ ተችሏል- የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም
አዲስ አበባ መጋቢት 25/2015 (ኢዜአ)፦ በበጀት አመቱ 9 ወራት የ4 ሺህ ግለሰቦችን አቤቱታ በመመርመር ችግራቸው እንዲፈታ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ መቻሉን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ገለጹ፡፡
በአገሪቷ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሳለጥና ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቁቁም ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደል እንዳይፈጸም አስቀድሞ በመከላከል ወይም ተፈጽሞ ሲገኝ በአፋጣኝ እንዲታረም በማድረግ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚሰራ መሆኑ ይታወቃል።
ተቋሙ በአስፈጻሚ አካላት የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደሎች ወይም የሕግ ጥሰቶች እንዲታረሙ በተቋሙ በኩል የመፍትሄ ሃሳብ በማስቀመጥ ጭምር ተፈፃሚ እንዲሆን አቅጣጫ ያስቀምጣል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ፤ በተቋቋመለት ዓላማ መሰረት ተቋሙ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም 15 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን በመለየት ከመልካም አስተዳደር መለኪያዎች እና ከውጤታማነት አንጻር የክትትል ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።
ከተጠያቂነት፣ ከህዝብ ተሳትፎና ከህግ የበላይነት አንጻር የክትትል ስራዎች በመከናወን ላይ ሲሆን ለተሻሉት ተቋማት እውቅና ሲሰጥ ችግር ያለባቸው ደግሞ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰዱ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የመንግስት የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የመከታተል ስራ በመስራት ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በበጀት አመቱ 9 ወራት በግለሰብ ደረጃ የ4 ሺህ ግለሰቦችን አቤቱታ በመመርመር ችግራቸው እንዲፈታ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ መቻሉን ዋና እንባ ጠባቂው ተናግረዋል።
በተለይም የጉልበት ብዝበዛና የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ረገድ ተቋሙ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ከተቋቋሙት የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታና ለሰብአዊ መበት መከበር እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።