"ለዘመናት ያቆየናቸውን የአብሮነት እሴቶች ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር መስራት አለብን"- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
"ለዘመናት ያቆየናቸውን የአብሮነት እሴቶች ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር መስራት አለብን"- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ መጋቢት 25/2015 (ኢዜአ)፦ "ለዘመናት ያቆየናቸውን የአብሮነት እሴቶች ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር መስራት አለብን" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
የረመዳን እና አብይ ፆም የጋራ የፀሎት መርሃ ግብር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ትውልዱ ፈጣሪውን የሚያከብርና ግብረ ገብነት የተላበሰ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"እኛ ኢትዮጵያውያን ከሚያለያየን ይልቅ አንድ የሚያደርገን ይበልጣል ፤ በደም የተቀላቀልን በመልክ የተወራረስን ጠንካራ የአብሮነት እሴቶች ያለን ህዝቦች ነን" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህ አኳያ የሃይማኖት አባቶች አብሮነታቸውን በማጠናከር ከምን ጊዜውም በላይ ለሰላም በጋራ መቆም እንዳለባቸው ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
የሃይማኖት ተቋማት በሀገር ግንባታ ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸውም ነው የጠቀሱት፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ሼህ ኢብራሔም ቱፋ በበኩላቸው ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ለአንድነት፣ ለሰላምና ይቅርታ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ መስራት አለብን ነው ያሉት፡፡
በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ኢትዮጵያ የተለያየ ብሔር ብሔረሰቦች እና ቤተ እምነቶች ተፈቃቅረው በሰላም የሚኖሩባት አገር ናት ብለዋል፡፡
"ሰላም ስላለ ነው ዛሬ በዚህ የተሰባሰብነው፤ በመሆኑም እኛ የሃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም መስበክ እና ማስተማር ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል "የአብሮነት እሴት እንዲጎለብት በዚህ መልኩ ማዕድ መቋደሱ ሚናው ከፍተኛ ነው" ብለዋል፡፡