የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ግብርናን ለማዘመን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ግብርናን ለማዘመን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አሶሳ መጋቢት 25/2015 (ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ግብርናን ለማዘመን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የፌደራል መንግስትና ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የበጋ ስንዴና ሌሎች የግብርና ሜካናይዜሽን እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በተጨማሪም የአሶሳ ግብርና ኮሌጅ ዘመናዊ የምግብ ማቀናባበሪያ እንዲሁም በአሶሳ ከተማ በማህበርና በግል የሚካሄዱ የወተት ላሞችና ዶሮዎች እርባታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣የኤርትራ፣የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮኔ በክልሉ ባዩት የሙከራ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአርሶ አደሩ ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑንና አርሶ አደሩ በግብርና ስራው ተገቢውን ድጋፍ ከተደረገለት ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለስኬት እንደሚበቃ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬትና የውሃ ሃብት አላት” ያሉት ዳይሬክተሩ በስንዴ ልማት የተገኘው ውጤት የሚሰሩ እጆች መኖራቸውን የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የስንዴ ልማት አጠናክራ መቀጠል እንደሚገባና በአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ በስፋት ወደ ውጪ ገበያ ማቅረብ እንደምትችል አመልክተዋል።
“የኢትዮጵያ ግብርና የበለጠ እንዲዘምን እንፈልጋለን” ያሉት ዳይሬክተሩ ለአርሶ አደሩ ትራክተር፣ ምርጥ ዘር እና የተለያዩ ግብዓት እንዲቀርቡ የዓለም ባንክ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በኢትዮጵያ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ገልጸዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በስንዴ የለማው መሬት ከ3 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ አስታውሰዋል፡፡
ከአርሶ አደሮች ተነሳሽነት ባሻገር በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በስንዴ ልማት ላይ ያሳዩት ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማስከበር አለባት ያሉት ሚኒስትሩ ክልሎች አሁንም ያላቸውን ለግብርና እርሻ የሚውለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ረገድ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሰፊ ለም መሬትና ውሃ ባለቤት መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ ካማሽ ዞን በኢትዮጵያ በአብዛኞቹ አካባቢዎች ምርጥ የበቆሎ ዘር በማቅረብ ያለውን እምቅ አቅም በበጋ ስንዴም እንዲደገም ሚኒስቴሩ የክልሉ አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ እንደሚደግፍ ነው ዶክተር ግርማ ያመለከቱት።
በቅርቡ የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በክልሉ ቅርንጫፍ እንደሚከፈትና ዓላማው የግብርና ሜካናይዜሽንን በተመጣጣኝ ዋጋ በስፋት በማቅረብ እየጨመረ የመጣውን የክልሉ አርሶ አደሮችን የግብርና ግብዓት ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ለመመለስ ነው ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ክልሉ ካለው እምቅ የመልማት አቅም የግብርናው ዘርፍ ተቀዳሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ የለማው 2 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ክልሉ ካለው አቅም አነጻር አነስተኛ ቢሆንም ተጨባጭ ተሞክሮ የተገኘበት ነው ብለዋል፡፡
ለተገኘው ውጤት የኦሮሚያ ክልል ምርጥ የስንዴ ዘርን ጨምሮ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
“ያለውን ለም መሬት ተጠቅመን በበጋ ስንዴ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ኤክስፖርት ለማድረግ ለተያዘው እቅድ ስኬት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት።
የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በክልሉ ለሚከፍተው ቅርንጫፍ ክልሉ በአጭር ጊዜ መሬት አዘጋጅቶ ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊውን ግብዓት እንደሚያቀርብ አመልክተዋል።