ዘመናዊ የመስኖ መሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው -የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ የመስኖ መሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው -የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ
ደብረ ማርቆስ መጋቢት 24/2015 (ኢዜአ ) በአማራ ክልል ዘመናዊ የመስኖ መሰረተ ልማት አውታር ግንባታዎችን በማስፋፋት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የተደራጁ ወጣቶች በመስኖ ልማት በመታገዝ በግብርናው ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያስችል ስልጠና መሰጠት ጀምሯል።
የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ እንዳሉት ክልሉ በመስኖ መልማት የሚችል 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬትና የውሃ ሃብት ያለው ነው።
ይሁን እንጂ ባለው ሃብት ልክ ለምቶ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን በተደረገ ጥረት በዘመናዊ መስኖ ግድቦች ከ230 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ የተገኘውን ፀጋ በእውቀትና ቴክኖሎጂ በማጎልበት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህም የዘመናዊ መስኖ መሰረተ ልማት አውታሮችን የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ በሚደገፍ ፕሮጀክት ወጣቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ የተጀመረው ስልጠና ወጣቶች በአዲስ ጉልበት ወደ ልማቱ እንዲገቡ የሚያግዝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በቅንጅት እንደሚሰራ አመልክተዋል ።
ፕሮጀክቱ በምስራቅ ጎጃም ዞን አዋበልና ደጀን ወረዳዎች በግንባታ ላይ በሚገኙ የጣቢትና ብልጭት መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰው ስልጠናው የሚሰጣቸው 100 ወጣቶች በዘመናዊ መስኖ ልማት እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።
"ወጣቶቹም አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶችን በማልማት ምርታቸውን ለቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያቀርቡ ይሆናል" ሲሉ አስታውቀዋል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ የወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጌታሰው መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት ግብርናን በማዘመን ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር ለመስኖ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች በመስኖ ግድቦች ላይ ወጣቶችን ለማሰማራት 102 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በጣቢትና ብልጭት የመስኖ ግድቦች ለሚሰማሩ ወጣቶች ከዛሬ ጀምር ለ12 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የውሃ ሀብት አያያዝ፣ የንግድ እንቅስቃሴና ከቅድመ እርሻ እስከ ድህረ ምርት አሰባሰብ ባለው ሂደት ስልጠና መሰጠት መጀመሩን አመልክተዋል ።
የምስራቅ ጎጃም ዞን መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አበበ ጓዱ በበኩላቸው በዞኑ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ መስኖ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።
የጣቢትና ብልጭት የመስኖ ግድቦች ከ418 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመው የመስኖ ግድቦቹ 2 ሺህ 600 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
"በመስኖ ግድቦቹ ስልጠና መውሰድ የጀመሩ ወጣቶችን በማሰማራት ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲያቀርቡ ይደረጋል" ብለዋል።
"ከዩኒቨርስቲ በአስተዳደር ዘርፍ ብመረቅም ስራ ሳላገኝ ቆይቻለሁ" ያለችው ደግሞ የአዋበል ወረዳ ነዋሪ ወጣት አስማረች ሞስነህ ናት።
አሁን ላይ በዘመናዊ መስኖ ልማት ለመሰማራት ስልጠና መጀመሯ መልካም መሆኑን ጠቅሳ፤ በቀጣይ የተገኘውን እድል በመጠቀም ውጤታማ ስራ ለማስራት እንደምትተጋ ገልፃለች።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ባገኘው ድጋፍ ስልጠናው መዘጋጀቱ ታውቋል ።