ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችንም የልማት ስራዎች በስኬት እንዲቀጥሉ ሀገራዊ ለውጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችንም የልማት ስራዎች በስኬት እንዲቀጥሉ ሀገራዊ ለውጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ
ሐረር መጋቢት 24/ 2015 (ኢዜአ)፡- ችግሮችን በመቋቋም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሀገራዊ ለውጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ።
"መጋቢት 24 የኢትዮጵያውያን የነፃነትና የእኩልነት ሃውልት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ የምስራቅ ሃረርጌ ዞን አመራሮችና አባገዳዎች በሐረማያ የፓናል ውይይት አካሂደዋል ፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በዞኑ የማያ ሲቲ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ፈዲላ ዳውድ ፤ለውጡ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮችን በመቋቋም የሀገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በአንድ ላይ በማስተሳሰር ጠንካራ ሀገረ መንግስት እንዲገነባ ማመቻቸታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል ይደርስ የነበረውን ጭቆናና በደል በማስቀረት ህዝቡን በቀጥታ በማሳተፍ የሀገር ባለቤት እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ተሰደው የነበሩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ውጤት የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳል አመራር ከነበሩበት ችግር በማውጣት በስኬት እንዲቀጥል ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል።
ለምርትና ምርታነት ትኩረት በመስጠት ከውጭ ይገባ የነበረውን ስንዴ በማስቀረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስኬት ማስመዝገባቸውንም አውስተዋል፡፡
የማያ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ኢፍራህ ወዚር በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበሳል አመራር ችግሮችን ተቋቁመው የጀመሩት የብልፅግና ጉዞ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን እንዲፈታ በማድረግ መላ አፍሪካውያንን ያስተማረ ታሪክ መስራቸውንም ተናግረዋል፡፡
የህዳሴው ግድብ ግንባታ በስኬት እንዲቀጥል እንዲሁም የተጓተቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ ብሎም አዳዲስም ተግባራዊ ማድረግ መጀመር መቻላቸው የሚያኮራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አወዳይ ከተማ ነዋሪ አባገዳ አህመዲን ሙክታር ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በተሳካ ሁኔታ ወደ ፍፃሜው እየተቃረበ መምጣቱን መስማታቸውና ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ተሸላሚ መሪ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ ላይ የነበረውን የአይቻልም መንፈስ በመስበር ለረጅም ጊዜ ከውጭ ስናስገባው የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ በማስቀረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ በመጀመሩ ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡
ካሁን ቀደም የነበረውን ኩረጃ በማስቀረት ለትምህርት ጥረት የሰጡት ልዩ ትኩረት ሀገሪቱን ከችግር ሊያወጡ የሚችሉ ትውልድን ለማፍራት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የመልማት እድል አለማግኘታቸውና ከለውጡ ወዲህ አካባቢያቸው እድሉን አግኝቶ በልማት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የማያ ሲቲ ነዋሪ አባገዳ ጀማል ሙሴ ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰል አመራር ሰጪነት በተጀመረው ልማት አሁን ላይ ተጠቃሚ መሆን በመጀመራቸው ፈተናዎችን በአንድነት ተቋቁሞ በማለፍ ለቀጣይ ጊዜ ስኬት ከጎናቸው እንደሚቆሙ አስታውቀዋል፡፡