ከሃኪም ትእዛዝ ውጭ መነፅር መጠቀም የዓይን ህመምን ወደ ከፋ ደረጃ ከማሸጋገር ባለፈ ለዓይነ-ሥውርነት ሊዳርግ ይችላል- የህክምና  ባለሙያዎች  

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2015 (ኢዜአ) ከሃኪም ትእዛዝ ውጭ መነፅር መጠቀም በቀላሉ ሊድን የሚችልን የዓይን ህመም ወደ ከፋ ደረጃ ከማሸጋገር ባለፈ ለዓይነ-ሥውርነት ሊዳርግ የሚችል መሆኑን የህክምና  ባለሙያዎች ተናገሩ።

የዓይን ህመም በመታከምና በሃኪም ትእዛዝ በሚደረግ መነፅር መስተካከል የሚችል ቢሆንም ብዙዎች ይህንን ባለማድረግ ለከፋ ችግር ሲዳረጉ ይስተዋላል።

ከአቧራ፣ ጸሐይና መሰል ጉዳቶች ዓይንን ለመጠበቅ በሚል ያለ ሃኪም ትእዛዝ የሚደረጉ መነፅሮች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝን በመሆኑ "አትጠቀሙ" ሲሉ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በአለርት አጠቃላይ ልዩ ሆስፒታል የዓይን ክፍል ሃላፊ ዶክተር ሰለሞን ቦሳ፤ ከሃኪም ትእዛዝ ውጭ የተገኘውን ሁሉ መነጽር ማድረግ የከፋ ችግር የሚያስከትል መሆኑን ይናገራሉ።

በቀላሉ ሊድን የሚችልን የዓይን ህመም ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋገርና ለዓይነ-ሥውርነት ሊዳርግ የሚችል ስለመሆኑም ያስረዳሉ። 

በመሆኑም አይንን ከጉዳት ለመታደግ በተለይም መነጽርን በሃኪም ትእዛዝ ብቻ ፈቃድ ካለው የመነጽር መሸጫ ገዝቶ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ።

ይሁንና ከሀኪም ትእዛዝ ውጭ ያገኙትም መነጽር እያረጉ የሚሄዱ ከሆነ ለከፋ የአይን ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉና ከዛ ባለፈ ለአይነ ስውርነት ሊዳርጋቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ለጸሃይ ብርሃንና ለአቧራ መከላከያ እየተባሉ ከተገኘበት ቦታ ሁሉ ተገዝተው የሚደረጉ መነጽሮች የአይን የጉዳት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉም አብራርተዋል።


 

በሆስፒታሉ የዓይን ህክምና ክፍል ጠቅላላ የዓይን ሀኪም ዶክተር ቤዛ ውቤ፤ በበኩላቸው የበርካቶች የዘፈቀደ መነፅር ገዝቶ መጠቀም በአይናቸው ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሃኪም ትእዛዝን ብቻ በመከተል አይንን መታከምና ከጉዳት መጠበቅ እንደሚገባ መክረዋል።

ማንኛውም ሰው መነፅሮችን ማድረግ ያለበት በሃኪም ትእዛዝ ብቻ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት ዶክተር ቤዛ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም