በሀገር ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2015 (ኢዜአ)፦ በአገር ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የምስረታ መርሃ -ግብር ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በሁሉም መስክ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ በርካታ ወጣቶችን ከያዙ አገራት መካከል ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠች መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ወጣቶችን በሁሉም ዘርፍ ማሳተፍና ተጠቃሚ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግስት የወጣቱን አገር የማልማት አቅም ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሂደቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ የልማት ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት መቋቋሙ የላቀ ፋይዳ አለው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወጣት ፉአድ ገና፤ "የወጣትነት እድሜ በትክክል ስራ ላይ ሲውል ከራስ አልፎ ለአገር የሚጠቅም በመሆኑ በሁሉም መስክ የጋራ አሻራዎቻችንን እያኖርን ለመጓዝ ተዘጋጅተናል" ብሏል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በይፋ መመስረቱ ለአገር ልማትና እድገት እንዲሁም የወጣቶችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ያሏቸው መሆኑን የተናገረው ፕሬዝዳንቱ ጥያቄዎችን ወደ አንድ ቋት በማስገባት በነጻነትና በሃሳብ የበላይነት ለማስተላለፍ የምክር ቤቱ እውን መሆን ምቹ እድል ይፈጥራል ብሏል። 

የምክር ቤቱ መመስረት ከአገር አልፎ በአህጉሪቷ የፓናፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን በማጠናከር ሂደት የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ተናግሯል።


 

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ በአገር ልማት የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በመሆኑም ወጣቶች ኢትዮጵያን በማልማትና ለህዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን በማከናወን ዘመን የሚሻገር ታሪክ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የወጣትነት ጊዜ እምቅ አቅም፣ ሃይልና የለውጥ ፍላጎት ያለበት በመሆኑ በተባበረ ክንድ ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት "ለወጣቶች ድምጽ" በሚል መሪ ሃሳብ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሚመለከታቸው አካላትና ከሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የተወጣጡ ወጣቶች በታደሙበት በይፋ ተመስርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም