ሰላምና ዴሞክራሲን ለማፅናት በአንድነት በመቆም የድርሻችንን እንወጣለን- የአዳማ ከተማና ምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምና ዴሞክራሲን ለማፅናት በአንድነት በመቆም የድርሻችንን እንወጣለን- የአዳማ ከተማና ምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች
አዳማ መጋቢት 24 /2015(ኢዜአ)፡- ሰላምና ዴሞክራሲን በማፅናት የለውጡ ቱሩፋቶችን ለመጠበቅ በአንድነት በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ የአዳማ ከተማና የምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ።
ከአዳማ ከተማና ከምስራቅ ሸዋ ዞን ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመደገፍ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄደዋል።
ነዋሪዎቹ በአዳማ ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ ድጋፋቸውን የገለጹት ባነገቡት መፈክርና በሰጡት አስተያየት ነው።
ከድጋፍ ሰልፍ ታዳሚዎች መካከል በአዳማ ከተማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ገኖ አብዱቃድር በሰጡት አስተያየት፤ መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ህዝቦች ድርብ ድል ያስመዘገቡበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል ።
ለውጡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን አንድነት ያፀናና እንድንደማመጥ ያስቻለን ነው ያሉት ወይዘሮ ገኖ፤ የተገኘውን ድል እየጠበቅን ለውጡን እናስቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል።
ፅንፈኝነት አንድነትን የሚንድ በመሆኑ አጥብቀን እንታገላለን ብለዋል ።
ሁሉም ከጎረቤቱና አካባቢው ጀምሮ ሰላምን ማስጠበቅ እንዳለበት አመልክተው፤ ሰላም ለመንግሥትና ለፀጥታ አካላት የሚተው ሳይሆን ሁላችንም በአንድነት መጠበቅ አለብን ነው ያሉት።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የአዳማ ወረዳ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ያሚ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳል አመራር የተገኙ የለውጡ ቱሩፋቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለመደገፍ በሰልፉ መታደማቸውን ተናግረዋል።
ለውጡ ተስፋ ሰጪና ሀገሪቱን ወደ ፊት ያራመደ በመሆኑን ይሄንን አጠናክረን ለማስቀጠል ዝግጁ ነው ብለዋል ።
የለውጡን ጉዞ አምስተኛ ዓመት ስናስብ በተለይ በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በልማት የተገኙትን ውጤቶች ከመንግስት ጎን ሆነን ማስቀጠል አለብን ያለው ወጣት ሰባፋን ሁሴን ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳል አመራር በሀገር ደረጃ የተገኘው ድል ለማስቀጠል በአንድነት እንታገላለን ብሏል ።
ሰላምና ዴሞክራሲን በማፅናት የለውጡ ቱሩፋቶችን ለመጠበቅ በአንድነት በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር፤ ለውጡ በፖለቲካው ከተገኘው ድል ባለፈ በተለይ ስንዴን በራስ አቅም በስፋት በማምረት እራስን ለመቻል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ ብሔር ብሔረሶቦች ከአስተዳደሩ ጋር በአንድነት ሆነው ሰላማቸውን ከማስጠበቅ ባሻገር የለውጡን ቱሩፋቶች በማስቀጠል ረገድ ድንቅ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አሁንም ለውጡ ያስገኘልንን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎችን አጠናክረን በማስቀጠል ሰላምና ዴሞክራሲን በአንድነት ማፅናት አለብን ብለዋል ።
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው፤ መጋቢት 24 እውነተኛ ፌዴራልዝምና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት እንዲረጋገጥ ያስቻለ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጽንፈኝነት በመታገል አንድነት፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ሰላምን በተባበረ ክንድ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የለውጡ አመራር በሰጠው በሳል አመራር በሀገር ላይ የተደቀነውን የሉዓላዊነት አደጋ በብቃት መመከት መቻሉን አውስተው፤ ለውጡ እያስገኘ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድል አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።
የኦሮሞ ህዝብ ወደ ነበረበት የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴትና ባህሉ እንዲመለስ የባህል ፍርድ ቤቶች መደራጀታቸውንና "ቡሳ ጎኖፋ " መቋቋሙን ጠቅሰዋል።
በዚህም ህዝቡ ፈጣን ፍትህ እንዲያገኝ መቻሉን ጠቁመው፤ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋን ለመቋቋም አቅም እንዲገነባ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም አመልክተዋል።
አሁንም በዞኑና በከተማዋ አስተማማኝ ሰላምን በአንድነት በማፅናት የለውጡን ድሎች ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሻገር ይገባናል ሲሉ አቶ አባቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።