የሽግግር ፍትህና የአፍሪካውያን ተሞክሮ

3012

የሽግግር ፍትህና የአፍሪካውያን ተሞክሮ 

በሰለሞን ተሰራ

በታሪክ ተመዝግበው የምናገኛቸው አያሌ መልካምና በጎ ነገሮች የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ደግሞ የሰው ልጆች ግፍና በደል ሲፈጽሙና ሲያስተናግዱ ኖረዋል።

በዚህም በተለይ በበደሉ ገፈት ቀማሾች ላይ የሚደርሰው ድንጋጤ፣ ሰቆቃና ሀዘን ሰዎችን ለበቀል እያነሳሳ ሌላ ጥፋት ሲያስከትል ማስተዋልም እንግዳ ነገር አይደለም።

በዚያው ልክ ሰዎች የደረሰባቸውን ግፍና መከራ ለማራገፍ ፍትህን ሲሹና ሲጠይቁ ይስተዋላል። እምባቸው የሚታበሰው፣ ቁስላቸው የሚሽረው ለደረሰባቸው በደል ካሳ የሚሆን ፍትህ ሲያገኙ ብቻ እንደሆነም ያምናሉ።

በርካታ አገራትም በታሪክ ውስጥ ላጋጠሟቸው ስብራቶች የሽግግር ፍትህን አማራጭ አድርገው በመጠቀም ለችግሮቻቸው መፍትሄ ያበጃሉ።

እኤአ በ1970 ዎቹ መጀመሪያ በምስራቅ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ተግባራዊ በተደረገው የሽግግር ፍትህ በጦርነትና በግፍ አገዛዝ የተበደሉ አካላት ፍትህ እንዲያገኙ የተደረገበት መንገድ ተጠቃሽ ነው።

ከዚህ ጊዜ በኋላ የሽግግር ፍትህ በተለይ በመደበኛ የህግ ስርአት ብቻ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስቸግሩ ጉዳዮችን ጭምር በተጠያቂነት፣ በይቅርታ፣ በካሳ ወዘተ መፍትሄ በመስጠት የፍትህ ማስፈኛ መንገድ  ተደርጎ ተወስዷል።

የሽግግር ፍትህ ማለት በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጥበት አካሄድ መሆኑን ምሁራን ያስረዳሉ። ይህንን ሂደት ሰላማዊ፣ አካታችና ተደራሽ ለማድረግ የሁሉም ጥረትና አጋርነት ቀዳሚ መነሻ ሊሆን እንደሚገባውም ይገልጻሉ።

የሽግግር ፍትህ በአንድ ጊዜ የሚያልቅ ሳይሆን ጊዜ የሚጠይቅና ዓመታትን ሊወስድ የሚችል ነው። ይህም ለተበዳዮች ፍትህ በመስጠት፣ ካሳ በመክፈል፣ የወደሙ ንብረቶችን መልሶ በመገንባትና በመሰል ሂደቶች ሊፈጸም ይችላል።

የሽግግር ፍትህ ሀገራት ከብጥብጥ፣ ከፀብና ጥላቻ አዙሪት እንዲወጡ በማድረግ በኩል የማይተካ ሚና እንዳለው የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች ያሳዩናል።

በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የፀደቀው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍ፣ የሽግግር ፍትህ  ሀገራት የተለያዩ መደበኛ እና ባህላዊ ወይም መደበኛ ያልሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችንና ተቋማዊ አሠራሮችን በመጠቀም የተፈጸሙ ጥሰቶችን፣ ክፍፍሎችንና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድና ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚደረግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ሂደት እንደሆነ ይገልጻል።

የሽግግር ፍትህ በግጭት፣ በጦርነት ወይም ጨቋኝ ሥርዓት በነበረበት ወቅት ለተፈፀመ ጥቃት፣ መጠነ-ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በደል የተሟላ መፍትሄ መስጠት መቻል ነው። 

ይህም በዋናነት ሙሉ ፍትህ የሚሰጥበትን መንገድ በመዘርጋት ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ፣ መረጋጋት እና የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መገንባት የሚቻልበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበውና በፖሊሲ አማራጭ ዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው የሽግግር ፍትሕ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች አስፈላጊ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል። 

 አንደኛው ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሀገራዊ አውድ ሲሆን በዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አለመረጋጋት፣ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት ተከስቷል። ይህም ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል ያጋለጠ መሆኑ በገፊ ምክንያትነት ይጠቀሳል። ለነዚህ ችግሮች ከዚህ በፊት የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆናቸው የአጥፊዎችና የተጎጂዎችን ቁጥር ማብዛቱ፣ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማህበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል ማለቱ የሽግግር ፍትህ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል።   

ሁለተኛው የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ማለትም ባለፉ በደሎች ይቅር ለመባባል፣ እርቅ ለማውረድ፣ ሕዝብ ለማቀራረብ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ለተፈጸመ በደል እውቅና ለመስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

ሶስተኛው ምክንያት የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ሳይተገበር የዴሞክራሲ ሽግግርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ማስፈን አይቻልም የሚል ነው።

የመጨረሻው በገፊ ምክንያትነት የሚጠቀሰው ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ወሳኝ በመሆኑ ነው።

ኢትዮጵያ በነዚህ ምክንያቶች የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን እየሰራች መሆኑ በበርካቶች ዘንድ በአዎንታዊ መልክ ይጠቀሳል። በተለይ የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ካደረጉ አገራት ተሞክሮ በመውሰድ ለውጤታማነቱ ከተሰራ በርግጥም አይነተኛ መፍትሄ ነው። 

ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ በቅርቡ ደግሞ ጋምቢያ የሽግግር ፍትህን ለችግሮቻቸው መፍቻነት ከተጠቀሙ አገራት መካከል ናቸው።

ሩዋንዳ

ሩዋንዳ እኤአ በ1994 በመቶ ቀናት ብቻ ከነበሯት 7 ሚሊዮን ዜጎቿ 800 ሺዎቹን በግፍ ተነጥቃለች። 2 ሚሊዮን የሚጠጉት በስደት ሀገራቸውን ለቀው ሲወጡ በዚህ የጭካኔ ተግባር ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ላይ ክስ በመመስረት ፍትህ ፊት አቅርባቸዋለች።

በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በሀገር ውስጥ ችሎትና በባህላዊ መንገድ በተዳኙት ወንጀለኞች ላይ የተሰጡት የፍትህ ውሳኔዎች አሁን ላይ ሀገሪቱን በዲሞክራሲና በሰላም እንዲሁም በብልፅግና መንገድ መራመድ እንድትችል አድርጓታል።

ሩዋንዳውያን በቆየ ሀገራዊ ብሂላቸው ”ሁላችንም የአንድ አባትና እናት ልጆች ነን ይላሉ”። ይህንኑ ብሂል መመሪያቸው በማድረግ በሀገሪቱ ያሉት “ቱትሲ” እና “ሁቱ” የተባሉት ዋነኛ ብሄሮች በአብሮነት ለዘመናት ኖረዋል።

ሩዋንዳ በጀርመን የቅኝ አገዛዝ ስር እንደወደቀች የዘር ልዩነቱን ወደፊት ያመጡት ቅኝ ገዥዎች ሁለቱን ብሄሮች የሚያጋጩ ሴራዎችን በመጎንጎን ቱትሲዎችን መግደል የፖለቲካቸው ስልት ማስፈጸሚያ አደረጉት። ይህ ከፋፋይ የፖለቲካ ሴራ በቤልጂየም የእጅ አዙር አገዛዝ ዘመንም እንደቀጠለ ይነገራል።

በዚህም ማንነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጃት፣ የመታወቂያ ወረቀት፣ ቱቲስዎችን በስልጣን ወደፊት ማምጣትና ሁቱዎችን አሳንሶ መመልከትን ባህል አደረጉት።

በዚሁ መርዘኛ ሀሳብ መነሻነት ከነጻነት በኋላ እኤአ ከ1959 እስከ 1967 አካባቢ በመንግስት በተደገፈ የዘር ማጥፋት 20ሺ የሚጠጉ ቱትሲዎች ሲገደሉ 300ሺ የሚጠጉ ሀገራቸውን ለቀው ተሰደዱ።

በዚህም እኤአ በ1987 በቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች የተቋቋመው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር እኤአ በ1993 የመንግስትን ስልጣን ለመጋራት በቃ። 

ነገር ግን እኤአ በሚያዚያ 6 ቀን 1994 የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ሃባይሪማና በቅጥረኞች በመገደላቸው በሀገሪቱ አመጽ እንዲቀጣጠል ምክንያት ሆነ።

ይህን ተከትሎ “ኢንተርሀሞይ” በመባል የሚጠራው የሚሊሽያ ቡድን በቱትሲዎችና በለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ ዘመን የማይሽረው ግፍና ጭካኔ በመፈጸም 800ሺ የሚጠጉትን ከምድር ላይ ለዘለአለሙ አሰናብቷቸዋል።

ይህ ደግሞ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሆኑ አጥፊዎቹ በተለያዩ የፍትህ አደባባዮች ተከሰው ቅጣታቸውን ለመቀበል በቅተዋል።

ነገር ግን ይህ ብቻውን በህዝቡ ውስጥ ስር የሰደደውን ቁስል እንዳማይሽረው በመታመኑ ሩዋንዳ የሽግግር ፍትህን በመከተል አመርቂ ስራ ሰርታለች። በተለይም ክስና ይቅርታ ትልቅ ቦታ ነበራቸው።

በክስ ሂደቱ ሁሉንም ተጠያቂ ማድረግ ቢከብድም በዋናነት ተሳታፊ የነበሩትን በመለየትና ተጠያቂ በማድረግ ፍትህ እንዲሰፍን ተደርጓል። መንግስት ውጫዊና ውስጣዊ ግፊት ቢበዛበትም ከፍተኛ ግፍ የፈጸሙትን በመለየት እንዲቀጡ አድርጓል። 

ይቅርታውንም በተጠና መንገድ በማከናወን ለጥቂቶች ምህረት አድርጓል። በጊዜ ሂደት የእስራት ጊዜአቸውን ላገባደዱ፣ ለአዛውንቶች፣ ለታማሚዎችና ለወጣቶች ምህረት በማድረግ ቁርሾው እንዲሽር ተደርጓል።

ምህረት የተደረገላቸው ሰዎች ስለብሄራዊ እርቅ፣ አብሮነት፣ ሀገራዊ ማንነትና ሰብዓዊ ክብር እንዲማሩ በማድረግ እርቁን ሙሉ ማድረግ ተችሏል።

የሩዋንዳ የሽግግር ፍትህ በዋናነት እውነትን ማፈላለግ፣ ነገሮችን መልሶ ማስታወስ ወይም የመታሰቢያ ቦታዎችን በመመስረትና ቀን በመሰየም ሁኔታው ታስቦ እንዲውል ማድረግ፣ መልሶ ማቋቋምና እርቅ ማውረድ የተቋማት ማሻሻያ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር።

ሴራሊዮን

እኤአ ከ1991 አስከ 2002 የዘለቀው የሴራሊዮን የእርስ በርስ ግጭት በትንሹ የ100ሺ ሰዎችን ህይወት ቀጥፎ አልፏል። ሌሎች በ100ሺ የሚቆጠሩ ዜጎችን ለከፋ የአካል ጉዳት፣ ድህነትና የአዕምሮ መቃወስ ዳርጓል።

ግጭቱ የተጀመረው ራሱን “የተባበሩት አብዮታዊ ቡድን” ብሎ በሚጠራው የታጣቂዎች ስብስብ ሲሆን በወቅቱ ቡድኑ በላይቤሪያ መንግስት ይደገፍ እንደነበር ይነገራል። 

የተቃውሞአቸው መነሻ ደግሞ የመንግስት ብልሹ አስተዳደር፣ የገጠሩ ማህበረሰብ ከኢኮኖሚና ፖለቲካ ተሳትፎ መገለል እና መጠነ ሰፊ የህግ ጥሰቶች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።

የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት በተለይም የአልማዝ ማዕድኗን በህገወጥ መልኩ ሲበዘብዙ የነበሩ አመራሮች ቁርሾውን በማባባስ ህልውናቸውን ለማስቀጠል ቢጥሩም እኤአ በ2002 በተደረሰ የሰላም ስምምነት ከ 76 ሺ ያላነሱ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን በማስረከብ ህብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል።

በዚያው ዓመት የሴራሊዮን የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን የተቋቋመ ሲሆን በተመሳሳይ የሴራሊዮን ልዩ ችሎት ተመስርቷል።

ሴራሊዮን በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ በነበረችባቸው 12 ዓመታት አራት መፈንቅለ መንግስት የተካሄደባት ሲሆን የስልጣን መንበሩን የተፈራረቁበት የተለያዩ ወታደራዊ አመራሮች ለችግሩ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ በቤንዚን ላይ እሳት የሚያርከፈክፉ ሆነው ታይተዋል።

በሴራሊዮን ለደረሰው እልቂት እኩል ኃላፊነት የሚወስዱት መንግስትና ታጣቂዎች በወቅቱ ሴቶችን በመድፈር፣ ህፃናትን በግዳጅ ለጦርነት በመመልመል፣ ንብረት በማውደምና በ100ሺ ለሚቆጠሩ ሰዎች መሞት ተጠያቂ ተደርገዋል።

ከዚህ ባለፈ በቅድሚያ ታጣቂዎችን የጦር መሳሪያ ለማስፈታት የተሄደበት ርቀት ለሰላም መስፈን ትልቅ እገዛ ማድረጉ የሚገለጽ ሲሆን ከ70 ሺ ያላነሱ ታጣቂዎችን መሳሪያ ማስፈታት መቻሉ ግጭቱን ለማስቆም በራሱ ታላቅ ስኬት ነበረው። 

በወቅቱ ግፉን የፈጸሙት ታጣቂዎች በመንግስት ቅጣታቸውን እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን ህብረተሰቡም ወንጀለኞችን ከማህበረሰቡ በማግለል የስነ ልቦና ቅጣት እንደጣለባቸው መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህም ታጣቂዎቹን ወደ ህብረተሰቡ መልሶ ለመቀላቀል የተደረገው ጥረት በፈተና ቢታጀብም በህዝቡ ይሁንታ ውጤታማ ሆኗል።

በሴራሊዮን የሽግግር ፍትህን ለማስፈን የተቋቋሙት የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን፣ የሴራሊዮን ልዩ ፍርድ ቤት፣ በፀጥታ ተቋማት ላይ የተደረገው ማሻሻያ፣ የመልሶ ማቋቋምና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምስረታ ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው።

የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተጎጂዎችን ከሰቆቃ መታደግና ችግሩን በዕርቅ መፍታት፣ ብዙሀኑ ላይ ለደረሰው ግፍ ምላሽ መስጠት፣ ግፉ በቀጣይ እንዳይደገም መፍትሄ ማበጀት ላይ አተኩሮ ሰርቷል፡፡

በዚህም ከተጎጂዎች ቃለ ምልልስ በመነሳት በደረሰበት ድምዳሜ የመንግስት አካላት የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ ሙስና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከነፃነት በኋላ የነበረው አመራር ብቃት ማነስ ለብጥብጡ መንስኤ እንደሆነ አመላክቷል።

ልዩ ፍርድ ቤቱም በቅድሚያ ተጎጂዎችን ሰብስቦ በማናገር እንዲሁም የሲቪል ማህበራትን ህብረተሰቡንና መገናኛ ብዙሃንን በማካተት ሁሉንም የሚያስማማ ውሳኔ በመስጠት ችግሩ ከቂም በቀል በፀዳ መልኩ መፍትሄ እንዲያገኝ አስችሏል።

የመልሶ ማቋቋም ሂደቱ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበርና ልዩ በጀት በመመደብ የተከናወነ ሲሆን የተጎጂዎችን ሰቆቃ ሊጠግን በሚችል መልኩ መተግበሩንም ብዙዎች ይመሰክራሉ። በዚህም ተጎጂዎች ነፃ የጤና አገልገሎት፣ ትምህርት፣ መኖሪያ ቤትና መቋቋሚያ እንዲያገኙ ተደርጓል።

በአብነት የተነሱት የሩዋንዳና ሴራሊዮን ተሞክሮዎች የሽግግር ፍትሕ መልከ ብዙ ግጭቶችን ያስተናገዱ ሀገራት የተሻለ ነገን እንዲገነቡ ሁነኛ መፍትሔ ስለመሆኑ አመላካች ናቸው። በተመሳሳይ የሽግግር ሂደት ያለፉና ተሞክሮ ያላቸው የደቡብ አፍሪካ እና ጋምቢያ ምሁራንም ይህንኑ እውነት የሚያረጋግጥ ሀሳባቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል። 

በደቡብ አፍሪካው ፍሪታውን ዩኒቨርሲቲ የፍትሕና ዕርቅ ኢንስቲትዩት ኃላፊ እና በአፍሪካ ጥናትና ምርምር የካበተ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ቲም ሙሪቲ በአፍሪካ ሽግግር ፍትህ ዙሪያ ጥልቅ ምርምር አድርገዋል። ኢትዮጵያ ታሪካዊና የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር ናት የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ የገጠማትን ችግር ለመፍታት የሽግግር ፍትህ ሂደት መጀመሯን አድንቀዋል።

የሽግግር ፍትሕ መልከ ብዙ ግጭትና ግፎችን ባሳለፉ ማህበረሰቦች  ትናንትን በይቅርታ የነገውን  ተሰፋ ለመሻገር  አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ፣ ባርነት እና ቅኝ ግዛት የጭቆና ስርዓት ነጻ ስትወጣ ስርዓቱ በጥቁሮች ላይ ለፈጸመው ግፍ፣ መገለልና ብዝበዛ መፍትሄ ለመስጠት ሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበሩን ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰር ሙሪቲ፤ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ በጥቁሮች ላይ የተፈጸሙ በደሎችን በሽግግር ፍትህ ሂደት መልክ ለመስጠት ብሎም ህዝባዊ አብሮነት እንዲቀጥል በሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ መሪነት የዕውነትና ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን መቋቋሙን ያስታውሳሉ።

የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከአፈጻጸም ጋር የተያያዙ  ክፍተቶች  ቢኖሩበትም አካታችና የአገሪቱን የቀጣይ ጉዞ ለመቀየስ መሰረት የጣለ እንደነበር ገልጸዋል። ይህም ኢትዮጵያ ተሞክሮ ልታደርገው የምትችለው ነው ይላሉ።

በጋምቢያ በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜህ ዘመነ መንግስት ለ22 ዓመታት የተፈጸሙ ግፎችን በሽግግር ፍትህ ሂደት የፈቱት የዕውነት፣ ዕርቅና ካሳ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ጋምቢያዊው ዶክተር ባባ ጋሌህ ጃሎው፤  የሽግግር ፍትህ አስፈላጊነት በተለይም ኢትዮጵያን ለመሰሉ ሀገራት አጠያያቂ አለመሆኑን ይላሉ።

በተመሳሳይ በጋምቢያ አምባገነን መንግስት የተፈጸሙ በደሎችን መልክ ለማስያዝ የተቋቋመው የዕውነት፣ ዕርቀ ሰላምና ካሳ ኮሚሽን ዜጎች ዕውነቱን እንዲረዱ፣ በዳዮች እንዲጠየቁና ተበዳዮች እንዲካሱ የሚያስችል ሰነድ ለሀገሪቷ መንግስት ማቅረቡን ዶክተር ባባ ጋሌህ ይገልጻሉ።

እነዚህ ምሁራን ኢትዮጵያ ለማድረግ ያሰበችው የሽግግር ፍትህ ሂደት ከአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ፍትሕ ፖለሲ እና የሀገራትን ልምድ የቀመረ፣ አካታች፣ ተበዳዮችን የሚክስና ሀገርና ህዝብ ወደፊት በሚያሻግር አግባብ እንዲፈጸም አስተያየታቸውን ጠቁመዋል። ለዚህ ደግሞ ምሁራኑ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ለሚመለከተው አካል እንደሚያጋሩ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያውያን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በህዝቦች የተባበረ ክንድ ለውጥ በማምጣት አዲስ ምእራፍ የጀመርንበት፣ አዲስ መንግስት ስልጣን ተቀብሎ ያለፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በይፋ በማመን ይህንኑ ለማሻሻል ቃል የገባበት፣ የዲሞክራሲ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት የተጀመሩበት እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት የደረሱ በደሎችን በሽግግር ፍትህ ለማለፍ መንገድ የጀመርንበት ወቅት ላይ መሆናችን ይታወቃል።

የሽግግር ፍትህ የተበዳዮችን እምባ ከማበስ ባለፈ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ በማስቀመጥ ከቂም በቀል የጸዳ ትውልድ ለመፍጠርና ለአገረ መንግስት ግንባታ በጋራ ለመሰለፍ መፍትሄ መሆኑን ከላይ የተጠቀሱት አብነቶች ምስክሮች ናቸው።

ለአፍሪካ ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሄን የምታስቀድመው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ተሞክሮዎችን በመቀመር፣ ካለፈችባቸው መንገዶች ትምህርት በመውሰድ፣ ውጤታማ የሆነ የሽግግር ፍትህ ስርዓትን እውን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

የሽግግር ፍትሕ በተለይም በሽግግር ላይ ያሉ ሀገራት ህዝቦች ከነበሩበት ግጭት እንዲሁም ከደረሰባቸው  ግፍ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወጥተው ወደ አዲስ ሰላማዊ እና አብሮነት ጉዞ ለመጀመር የሚደረግ የፍትሕ ክዋኔ አይነት በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል። 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም