በኢትዮጵያ እየታረሰ ካለው መሬት 45 በመቶው በኩታገጠም የለማ ነው- የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየታረሰ ካለው መሬት 45 በመቶው በኩታገጠም የለማ ነው- የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ መጋቢት 24/2015 ( ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አጠቃላይ እየታረሰ ካለው 14 ሚሊየን ሄክታር መሬት 45 በመቶው በኩታገጠም የለማ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።
በለውጡ ዓመታት በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት የስንዴ ልማትን ጨምሮ በበቆሎና የጤፍ ምርት እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ባከናወነችው የላቀ አፈፃፀም ምርት ከውጭ ማስገባቷ ቀርቶ ለውጭ ገበያ ያቀረበችበት ታሪካዊ ምእራፍም ተከፍቷል።
በቀጣይም የግብርናው ዘርፍ የተሻለ ዕድገት የሚመዘገብበት እንዲሆን የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ከማጠናከር ባለፈ የክላስተር ልማት በስፋት የሚከናወን መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ከኢዜአ በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ እየታረሰ ካለው 14 ሚሊየን ሄክታር መሬት ባለፉት ሶስት ዓመታት 45 በመቶው በኩታገጠም የለማ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ለአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ሌሎችንም ግብአቶች ተደራሽ በማድረግ በሜካናይዜሽን ማልማት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።
በኩታገጠም የተደራጁና ያልተደራጁ አካባቢዎች ላይ ጥናት አድርጎ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ የክላስተር እርሻ በምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ለአብነት በመኸር በኩታገጠም ከለማ ስንዴ በአማካይ በሄክታር 34 ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰው በኩታገጠም ካልታረሰ መሬት የላቀ ምርት እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በኩታገጠም ከለማ የመኸር ስንዴ 4 ኩንታል በሄክታር ተጨማሪ ምርት በማግኘት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ በኩታገጠም ከሚለማው መሬት በሜካናይዜሽን የሚታረሰው 22 በመቶ ብቻ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በሜካናይዝድ እርሻ ላይ በቀጣይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በኩታገጠም የለማውን መሬት በሜካናይዜሽን በማረስ በግብርናው ምርት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በተግባር ታይቷል ብለዋል።
የግብርና ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆን እያገለገለ ሲሆን ከ70 በመቶ በላይ ዜጎችን ስራ ላይ ያሰማራ ዘርፍ መሆኑም ይታወቃል።