ከለውጡ ወዲህ ለሀገር መከታና ደጀን የሆነውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለማጠናከር በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሠራ ነው--ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

413

አርባ ምንጭ፣ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ) ከለውጡ ወዲህ ለሀገር መከታና ደጀን የሆነውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለማጠናከር በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሠራ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

በለውጡ ማግስት በልዩ ትኩረት የተጀመረውን ሪፎርም በማጠናከር የሰራዊቱን ህይወት የሚለውጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል


 

የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ለደቡብ ዕዝ አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ ግንባታዎችን ዛሬ አስመርቋል።

ከግንባታው መካከል የኮርና ሻለቃ ጠቅላይ የሠራዊት መኖሪያ ካምፕ ይገኝበታል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት፤ ከለውጡ ወዲህ ለሀገር መከታና ደጀን የሆነውን የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለማጠናከር በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ተወስዷል።

በተለይም የሀገርን ዳር ድንበርና የህዝብ ሠላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስን ኃይል ለሚመክት ሰራዊት የተሻለ ቦታ ማዘጋጀት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
 

ባለፉት ሁለት አመታት የሰራዊቱን ህይወት የሚለውጡ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በልዩ ትኩረት መከናወናቸውን ገልጸው፤ ዛሬ የተመረቀው የኮርና ሻለቃ ጠቅላይ መምሪያ አንዱ ማሳያ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

እንደሀገር የመጣውን የለውጥ ሂደት ያልፈለገው ኃይል መልኩን እየቀያየረ የሀገርን ሰላም ለመናድ ያደረገውን ሙከራ ለማክሸፍ ሰራዊቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል።

በተለይም በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠርና ግጭት በማባባስ ሀገር ለማፍረስ የተደረገውን ጥረት በማምከን ረገድ ሰራዊቱ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣቱን ገልጸዋል።


 

አንዳንዶች ያልተፈለገ መርዝ በህዝብ መካከል ከረጩና ለውጭ ኃይል ጭምር በር ከከፈቱ በኋላ ሰራዊቱን በወገንተኝነትና በብሄር ፍረጃ ይከሳሉ በማለት ገልጸው፤ ይህን ለማስቀረት ሀገርን የሚወክል ሰራዊት ለመገንባት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል ሠራዊቱ ጠንካራ ዝግጅት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ሰራዊቱ የክፉ ቀን ምሽግና የሀገር አለኝታ ነው ብለዋል።

ሀገርን ለመጠበቅ በተጠንቀቅ ላይ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስም ለማጠልሸትና ለማፍረስ መጣደፍ የጠላትነት ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ሰራዊቱ የታነጸበት ጀግንነት ዲሲፒሊንና ህዝባዊ ወገንተኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል።


 

መከላከያ ሰራዊቱ ከግዳጅ በሚመለስበት ወቅት ማረፊያ እንዲኖረው ለማስቻል የሚሰሩ ሥራዎች በልዩ ትኩረት የሚቀጥል መሆኑን ተናግረው ሁሉም የሚጠበቅበትን ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሪፎርሙ 10 ዓመት መሪ ዕቅድ እንደተመላከተው ሰራዊቱ በዘመናዊ ካምፕ እንዲኖር የማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ በበኩላቸው ሀገር የገጠማትን ፈተና እንድትሻገር እያደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዓለም አቀፍ ተልዕኮ አንጻር በቱሪኪዬ በደረሰው ርዕደ መሬት የደረሰውን አደጋ ለመቀልበስ ሰብአዊ ስራ ላይ በመሳተፍ ወደር የሌለው አጋርነት ማሳየቱን ተናግረዋል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የሰራዊቱን አቅም ከፍ ለማድረግ ግዳጅን በብቃት ከመወጣት ባሻገር ህይወት ለዋጭ ተግባራት ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ዘመናዊ አገልግሎት ሰጪ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመከላከያ መኮንኖች የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴና የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም