የነዳጅ ግብይቱን ወደ ዲጂታል በመቀየር በአቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል እየተሰራ ነው

ጋምቤላ፣ መጋቢት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የነዳጅ ግብይቱን ወደ ዲጂታል በመቀየር በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ። 

ባለስልጣኑ ከጋምቤላ ክልል የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት መመሪያዎችና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ተወያይቷል።

የባለስልጣኑ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ በውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ ነዳጅ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እየመጣ ቢሆንም በአቅርቦትና በስርጭት ችግር ለብክነት እየተዳረገ ነው። 

በነዳጅ ላይ በተካሄደ ከፍተኛ ቁጥጥር የነዳጅ ኮንትሮባንድን 70 በመቶ ያህል መቀነሰ መቻሉን ጠቅሰው፤ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የቤንዚን ኮንትሮባንድ ንግድ መኖሩን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለማስቀረት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የነዳጅ ግብይት ሰንሰለቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል በማድረግ በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል ግብይቱ በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ መተግበር መጀመሩን ጠቁመው፤ ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች ስራ ላይ የሚውል ይሆናል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቦቲዎችና በማደያዎች ላይ የርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ (ጂፒኤስ) በመግጠም የአቅርቦቱንና የስርጭቱን ሂደት ለመቆጣጠር እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ እስካሁን ከሶስት ሺህ በሚበልጡ ቦቲዎች ላይ ጂፒኤስ መገጠሙን ጠቁመዋል።

ከክልሉ ባለድርሻ አካላት በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት መመሪያ ዙሪያ ውይይት ማድረግ ያስፈለገው የጠራ ግንዛቤ በመፍጠር የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር በማለም እንደሆነ ተናግረዋል።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ኡሌሮ ኦፒዮው በበኩላቸው የነዳጅ የጥቁር ገበያ እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ለጥቁር ገበያ መስፋፋት ዋነኛው ምክንያት ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ለችርቻሮ በበርሜል ተቀድቶ መሄዱ እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህ ሁኔታ ነዳጅ ከተመኑ በላይ በእጥፍ በመሸጡ እንደሆነ አመልክተዋል።

አሁን ላይ ችግሩን ለመከላከል እየተደረገ ባለው የክትትልና የቁጥጥር ስራ በጀሪካንና በበርሜል በህገ ወጥ መንገድ ይዘው የተገኙ አካላትን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በጋምቤላ ከተማ ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በቆየው የውይይት መድረክ ከክልል እስክ ወረዳ የሚገኙ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ የጽህፈት ቤት አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የማደያ ባለንብረቶች ተሳትፈዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም