በድሬዳዋ አስተዳደር የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ ከድር ጁሃር

305

ድሬዳዋ፣ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)፦ በድሬደዋ አስተዳደር ጎርፍን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።


 

በከንቲባው የተመራ የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላት በጎርፍ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን ዛሬ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በጎርፉ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለማቋቋምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካላት ለመለየት ኮሚቴ ተዋቅሯል።

ከምልከታው በኋላ በአስተዳደሩ ባለፉት 15 ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስና ለመከላከል በሶስት ደረቅ ወንዞች ላይ የተሰሩት የመከላከያ ግንቦች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ከንቲባ ከድር ጁዋር ገልጸዋል

በተለይም በገጠር ቀበሌዎች 10 ዓመታት የተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ጎርፍ በማሳዎች ላይ ሲያደርስ የነበረውን ችግር በማቃለል ውሃውን ለመስኖ ልማት ማዋል ተችሏል ብለዋል።


 

በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች በማጠናከር የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የተቀናጀ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እየጣለ የሚገኘው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በከተማው የመጠጥ ውሃ መሠረተ ልማቶች፣ በጎርፍ መውረጃ ቦዮች፣ በጎርፍ መከላከያ ግንቦችና ማሳዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል

ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመጠገንና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል አስተዳደሩ ኮሚቴ አዋቅሮ መፍትሄ የሚሆኑ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ወርቅነህ የጎርፍ ስጋት ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር በመሆንም በጎርፍ የተበላሹና የተሰበሩ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመጠገን ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምስራቅና መካከለኛ ኦሮሚያ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል እየጣለ የሚገኘው ዝናብ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ነዋሪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም