መምህራን ትውልድን በመልካም ሥነ-ምግባርና በእውቀት ለማነጽ የሚያከናውኑትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

1526

 

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)፦ መምህራን ትውልድን በመልካም ሥነ-ምግባርና በእውቀት ለማነጽ የሚያከናውኑትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኦሮሚያ ክልል ጠየቀ።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ከመጋቢት 18 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም "የትምህርት ለውጥ ከመምህራን ይጀምራል" በሚል መሪ ሃሳብ የመምህራን ሳምንት ማጠቃለያ መርሃ-ግብር አካሂዷል።



 
በመርሃ ግብሩ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን በጡረታ የተገለሉትን ጨምሮ ለአመራሮች የሜዳሊያ፣ የገንዘብ ሽልማትና የሰርተፊኬት እውቅና ተሰጥቷል።
 
በእውቅና መርሃ ግብሩ በዘንድሮው አገር አቀፍ ፈተና ላይ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ለሰሩ የትምህርት ማህበረሰብ አካላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።
 
የክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት መምህራን አዲሱን ትውልድ በማነጽና የአገር ግንባታ ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
 
''የሁሉም ሙያዎች መፍለቂያ መነሻ የሆነውን የመምህርነት ተግባር እውቅና መስጠት አገርን ማክበር በመሆኑ ለመምህራን ትልቅ ክብር ይገባቸዋል'' ነው ያሉት።
 
በዚህም መሰረት ክልሉ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ለመምህራን የእውቅና ሽልማት በመስጠት ለባለሙያዎቹ  ያለውን ክብር ማሳየቱን ገልጸዋል። 


የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር በሪሶ ቶላ በበኩላቸው የሁሉም ሙያዎች ቀዳሚ የሆነው መምህርነት በመሆኑ ለባለሙያው ትልቅ ክብር መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል። 



 
ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና እውቅትን እንዲገበዩ መምህራን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በክልሉ የሚገኙ መምህራንን አቅም ለማሳደግ እንዲሁም ምቹ የኑሮ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ  ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
 
እውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው መመምህራን በበኩላቸው የተሰጠው እውቅና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
 
ለመምህራን ትኩረት መሰጠቱ የትውልድና አገር ግንባታ ላይም ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም