ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015 (ኢዜአ) ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈቱ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት ሕዝቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል።

ሕዝቡ በቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ በ8100 አጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስጦታ አካውንትና በሌሎች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ-ግብር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ስምንት ወራት ከተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ከ1 ቢሊዮን 41 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ነው ያረጋገጡት። 

ሕዝቡ የሚያደርገው ድጋፍ እንዲጎለብት በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም የግድቡ ግንባታ በመልካም የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

ከመጋቢት 16/2015 ዓ.ም ጀምሮ የገቢ ማሰባሰቢያ ለአንድ ወር የሚቆይ ንቅናቄ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው ኅብረተሰቡ በመርኃ ግብሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ጽህፈት ቤቱ የተለያዩ መርኃ ግብሮችን በማዘጋጀት ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም