በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ህፃናት ነፃ የልብ ሕክምና አገልግሎት ሰጡ

248

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015 (ኢዜአ) በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች ከዲቦራ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው 100 ህፃናት ነፃ የልብ ሕክምና አገልግሎት ሰጡ።

የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤኪ አባዱላ እንደገለጹት፤ ከግልና ከመንግስት የህክምና ተቋማት በመጡ በጎ ፍቃደኛ ሃኪሞች ለአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ህፃናት ነፃ የልብ ሕክምና አገልግሎት  ተሰጥቷል።


 

በፋውንዴሽኑ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ከ1ሺህ 500 በላይ ህፃናትና ታዳጊዎች ተመዝግበው የተለያዩ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ ዜጎችና ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው የጤና፣ የትምህርትና የሰብዓዊ መብት አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ከፍለው መታከም ለማይችሉ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ህፃናት ነፃ የልብ ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል።

ፋውንዴሽኑ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ እያስገነባ ያለውን ትምህርት ቤት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸው፤  በዘንድሮ ዓመትም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የፊዚዮቴራፒ፣ የሙያና ሕይወት ክህሎት ሥልጠና መጀመሩን ገልጸዋል። 

የፋውንዴሽኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሔዋን ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ዘመቻዎችን በማካሄድ 600 ለሚደርሱ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ታዳጊዎች የዓይንና ከአንገት በላይ ሕክምና ሰጥቷል።


 

ፋውንዴሽኑ በቀን ለ30 የአዕምሮ እድገት  ውስንነት ላለባቸው ህፃናት የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም ሰባት በሚደርሱ በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች 100 ለሚደርሱ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ታዳጊዎች የልብ ሕክምና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጇ ገለጻ የአዕምሮ እድገት  ውስንነት ያለባቸው ህጻናት ለልብ ህመም ተጠቂ በመሆናቸው ህመሙ እንዳለባቸው አስቀድሞ በመለየት ህክምናውን እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።  

በበጎ ፈቃድ ከተሳተፉ ሐኪሞች መካከል ዶክተር ሚካኤል ጥላሁን አንዱ ሲሆኑ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህፃናት እንደ ሌሎች ሰዎች የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት አላቸው፡፡


 

ይህም የሚሆነው ሁሉም መተባበርና መተጋገዝ ሲችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡ በተለይ ደግሞ የጤና ባለሙያዎች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዲቦራ ፋውንዴሽን በአቶ አባዱላ ገመዳ በ2011 ዓ.ም. ተመስርቶ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸውና ለሌሎች ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም