የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ አሰራሮችንና የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገለጸ

199

ጎንደር፣ መጋቢት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመተግበርና የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡


በዩኒቨርሲቲው የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ካህሌ ጀምበሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ እየተሳተፉ ለሚገኙ 2 ሺህ አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

ዩኒቨርሰቲው በመካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ለሚሳተፉ አርሶ አደሮች በሶስት ትራክተሮች የታገዘ 75 ሄክታር ኩታ ገጠም መሬት ለአርሶ አደሮች ማስረከብ ችሏል።


 

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ለሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂውን በማስተዋወቅ በቀጣይ ዓመት በትራክተር ለማረስ የሚያስችሉ አሰራሮች ማመቻቸቱን ነው ዶክተር ካህሌ የገለጹት፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች አርሶ አደሮቹ እያለሙት ላለው 700 ሄክታር መሬት ከ1 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በማሰራጨት ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባቋቋማቸው አራት የምርምር ጣቢያዎች በመታገዝ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር የተላመዱ ምርታማ የስንዴ ዝርያዎችን በመለየት አንድ ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ማቅረቡን አመልክተዋል፡፡

በተሻሻሉ አሰራሮች ታግዞ በስንዴ ሰብል ከለማው መሬትም 31 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ነው ዶክተር ካህሌ የጠቆሙት።   

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የእርሻ ትራክተሮችንና ግብዓቶች በወቅቱ በማቅረብ እያገዘ እንደሚገኝ  የተናገሩት  የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሃውልቱ ታደሰ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና ከ600 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ በዞኑ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ለተሳተፉ አርሶ አደሮች በማቅረብ ለመርሐግብሩ መሳካት ድጋፍ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ 

በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ታምራት ጎሹ በበኩላቸው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአንድ ሄክታር መሬት እያካሄዱት ላለው የስንዴ ልማት በትራክተር በማረስ እንዳገዛቸው ገልጸዋል።


 

ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ቢክስ ሞላ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባቀረበላቸው አንድ ኩንታል ማዳበሪያና 30 ኪሎ ምርጥ ዘር በግማሽ ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ካለሙት መሬት 20 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ጠቅሰው፤ ምርቱን ከሰበሰቡ በኋላም በወረዳው ለሚገኘው የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ለማስረከብ ስምምነት ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የዘንድሮ የበጋ ወራት 14 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል እየለማ እንደሚገኝና ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም