የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

1007

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)"የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቤት ጥያቄን ለመመለስ ሁሉን አቀፍ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባ አዳነች በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ለልማት ተነሺዎች 200 ቤቶችን አስረክበዋል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችም ማዕድ አጋርተዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን የቤት ችግር ለማቃለል የተለያዩ  ስራዎችን እያከናወነ ነው።    

ይህንንም ተከትሎ በመንግስትና በግል አጋርነት እስካሁን 20ሺህ ቤቶች መገንባታቸውን አንስተዋል።

አሁን ላይ ደግሞ 120ሺህ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ገልጸው፤ የነዋሪውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

በአዲስ አበባ ያለውን ሀብት በፍትሃዊነት የማከፋፈል ግዴታ አለብን ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ዜጎችን በእኩል የማገልገል ኃላፊነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመጠቆም።  

ዛሬ የቤት ቁልፍ ከተረከቡት መካከል የጉለሌና አራዳ ክፍለ ከተማ የልማት ተነሺዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል


 

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የቤት ቁልፍ ከተረከቡት መካከል የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ውዴ መኬ "ታማሚ ልጅ ይዤ አውላላ ሜዳ ላይ ወድቄ ነበር፤ ዛሬ ግን ቤት በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ" ብለዋል


 

በደረሰበት የመኪና አደጋ እግሮቹን ያጣው ወጣት ነብያት አሉላ ጫማ በመጥረግ አምስት ቤተሰቡን እያስተዳደረ መሆኑን ተናግሯል።  

"የነበርኩበት ቤት ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፤ ከመንግስት ያገኘሁት የቤት ስጦታ ሕይወቴን ለመቀየር መሰረት የሚሆን ነውብሏል።     


 

ዛሬ ለአቅመ ደካሞችና ለልማት ተነሺዎች የተከፋፈለው ቤት የተገነባው በባለሀብቶች ድጋፍ ሲሆን ስድስት ብሎኮች ያሉት ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም