በጣና ሐይቅ ላይ 1ሺህ 250 ሄክታር ስፍራ ሸፍኖ የነበረ የእምቦጭ አረም መወገዱ ተገለጸ

ባህር ዳር፣ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ) በጣና ሐይቅ ላይ 1ሺህ 250 ሄክታር ስፍራ ሸፍኖ የነበረ የእምቦጭ አረም መወገዱን የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በሐይቁ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች አረሙን ለማስወገድ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅ ጠይቀዋል። 

የአማራ ክልልና የዞን የስራ ኃላፊዎችና የግብርና ቢሮ ሰራተኞች የእምቦጭ አረም ማስወገድ ስራ ዛሬ አከናውነዋል።

የኤጀንሲው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ልየው እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ዓመት ብቻ በጣና ሐይቅ 2ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ቦታ በእምቦጭ አረም ተወሯል።

በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር፣ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ዞኖች በሚገኙ 35 ቀበሌዎች አረሙን የማስወገድ ስራ በሕዝብ ጉልበትና 10 ማሽኖች በመታገዝ የተቀናጀ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።


 

ባለፉት ሶስት ወራት የአካባቢውን ሕብረተሰብ በማሳተፍ በተደረገው ጥረት በሐይቁና በሐይቁ ዳርቻ 1ሺህ 250 ሄክታር ላይ የነበረ የእምቦጭ አረም ማስወገድ መቻሉንም ነው አቶ ዘላለም የጠቆሙት።

የእምቦጭ አረም ማስወገድ ስራ ውጤት እያመጣ እንደሆነና፤ በቀጣይ የእምቦጭ አረም ከሐይቁ የማስወገድ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ባለድርሻ ተቋማትም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው የጣና ሐይቅን ብዝሃ ህይወት በዘላቂነት መጠበቅ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ለሐይቁ ደህንነት ዋነኛ ፀር የሆነውን የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ቢሮው ከኤጀንሲው ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የሐይቁን ደህንነት በዘላቂነት ለመጠበቅ ሁሉም በእኔነት ስሜት የእምቦጭ አረምን በመከላከል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በፎገራ፣ ሊቦ ከምከምና ደራ ወረዳዎች በእምቦጭ አረም ከተወረረው 75 በመቶ የሚሆነውን ስፍራ ከአረሙ ማጽዳት መቻሉን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ተፈራ ናቸው። 

ቀሪውን አረም በቀጣይ ወራት ለማስወገድ በወረዳዎቹ የሚገኙ አርሶ አደሮችና አመራሮች በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም