በኦሮሚያ ክልል የጤና ተቋማት የ 'ዲጂታል' አገልግሎት ተጀመረ

324

አዳማ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የተገልጋዮችን እርካታ ያሳድጋል ያለውን የጤና ተቋማት 'ዲጂታል' አገልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ።

የአገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ በአዳማ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንግሥቱ በቀለ በክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት 41 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተመላላሽ ታካሚዎች አገልግሎት ተሰጥቷል።


 

'ዲጂታልአገልግሎቱ የተገልጋዩን ሕብረተሰብ እርካታ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል

በተለይም የእናቶችና ሕጻናትን ጤና ለመጠበቅና ፈጣን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

"በክልሉ በተካሄደው ጥናት የተገልጋዮች የአገልግሎት እርካታ 52 በመቶ ላይ ይገኛል" ያሉት ዶክተር መንግስቱ፣ የዲጂታል አገልግሎቱ ፈጣንና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳ አስረድተዋል።


 

አገልግሎቱ ደንበኞች ባሉበት ሆነው የጤና አገልግሎትን እንዲያገኙ እንደሚያስችል ኃላፊው አመልክተዋል

በክልሉ "አንዳንድ የግል ጤና ተቋማት ያልተመዘገበና ምንጩ ያልታወቀ መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ" እንደሚጠቀሙ አመልክተው፣ አገልግሎቱ ችግሩን ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል 26 ሚሊዮን ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ ሁሉም ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው ቢሮው የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማቃለልና የተገልጋዮችን እርካታ ለማሻሻል ተግባራዊ ያደረገው 'ዲጂታል' አገልግሎት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የጤና ተቋማት ተደራሽነትን፣ የባለሙያዎችን አቅም ከማጎልበትና የአገልጋይነት ስነ-ምግባር እንዲላበሱ ለማድረግ የጀመራቸውን ተግባራት እንዲያጠናክር አሳስበዋል።


 

የጤና ባለሙያዎች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የአቅርቦትና የተገልጋዮች እርካታን እውን ማድረግ ትኩረት የሚሹ ቀጣይ ስራዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የጤና ተቋማቱ በሚሰጡት አገልግሎት የሚረካ ማህበረሰብ ለመፍጠር በትብብርና በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባ ነው አቶ ነመራ ያሳሰቡት።

በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋን ያገኙ ዜጎች 26 ሚሊዮን መድረሱ በሴክተሩ የተመዘገቡ ስኬቶችን ያሳያል ያሉት አቶ ነመራ በተለይ በቴክኖሎጂ፣ በአዳዲስ አሰራርና አደረጃጀት የተደገፈ አገልግሎት ማስፋት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም