የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ሊመሰረት ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015 (ኢዜአ) የወጣቶችን ድምፅ ለማሰማት እንዲሁም መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚያስችል የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ሊመሰረት ነው። 

በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 31 በተቀመጠው በነፃ ፍላጎት የመደራጀት መብትን መሰረት በማድረግ በአገሪቱ የተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች ተፈጥረው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በነገው ዕለት አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ሊመሰረት መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል።


 

ምክር ቤቱ የወጣቶችን ድምፅ ለማሰማት እንዲሁም መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ዓላማ ያደረገ ሲሆን ጠንካራ የወጣት አደረጃጀት መመሥረት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የምክር ቤት ምስረታው መንግሥትን የማማከር ሚና ያለው፣ ሁሉንም የሚያሳትፍና አካታች እንዲሁም  ቅንጅታዊ  አሰራር ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በዚህም ሁሉም ወጣቶች በማንኛውም ልማት እንዲሳተፉና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከጠባቂነት ስሜት ወጥተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

ወጣቶች ጠንካራ አገራዊ የወጣቶች ምክር ቤት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጥሪ አቅርበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም