ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአካባቢውን አገራት በኃይል ለማስተሳሰር ያስችላል -- የቀድሞ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ኦስማን አል-ቶም ሃማድ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአካባቢውን አገራት በኃይል ለማስተሳሰር ያስችላል -- የቀድሞ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ኦስማን አል-ቶም ሃማድ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)፦ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአካባቢውን አገራት በኃይል ለማስተሳሰር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የቀድሞ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ኦስማን አል-ቶም ሃማድ ገለጹ።
የቀድሞ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትሩ ኦስማን አል-ቶም ሃማድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅ በመቆጣጠርና የውሃ ፍሰቱን በማስተካከል ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
በተለይም ሱዳን የውሃ ፍሰቱን በመቆጣጠር አገሪቱ ከሚገጥማት የጎርፍ አደጋ ይታደጋታል ብለዋል።
ጎን ለጎንም ተከታታይ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት ግድቡ ክስተቱን በመቋቋም የራሱ አዎንታዊ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ አተገባበሩ ድረስ በጥንቃቄ እየተገነባ ያለ ግድብ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ግድቡ ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት አገራቱ እርስበርስ እንዲተሳሰሩ ያስችላል ነው ያሉት።
በመሆኑም የአካባቢው አገራት ለጋራ ጥቅም መተባበር ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በውሃ ጉዳይ ተባብረው ከሚሰሩ ሌሎች አገራት ተሞክሮ መቀመር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአካባቢው አገራት ግድቡን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የልማት መስኮች ላይ የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
በጋራ ለመሥራትና ፕሮጀክቶችን ለመቅረጽ የአገራቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ።
በጋራ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የጋራ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ግቦችን ለማሳካት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
የጋራ የልማት ፕሮጀክቶቹ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙም በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
አገራቱ በሦስትዮሽ ማዕቀፍ በሚያካሂዱት ውይይት የሦስቱን አገራት ፍላጎት የሚያረጋግጥ ሥምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።