ከለውጡ በኋላ የተገኘውን ድልና ስኬት ለማስቀጠል ያለመ የድጋፍ ሰልፍ ነገ በመላው ኦሮሚያ ይካሄዳል--የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

305

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)-- ከለውጡ በኋላ የተገኘውን ድልና ስኬት ለማስቀጠል ያለመ የድጋፍ ሰልፍ ነገ በመላው ኦሮሚያ እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል በነገው እለት የሚካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ አስመልክቶ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ሀይሉ አዱኛ እንደተናገሩት፤ የድጋፍ ሰልፉ የሚካሄደው ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ወዲህ በክልሉ የተመዘገቡ ድልና ስኬቶችን ጠብቆ ለማስቀጠል ነው።

ከለውጡ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማሕበራዊና በሌሎች ዘርፎችከፍተኛ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ስለሆነም በነገው እለት በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ ህዝቡ ድልና ስኬቶችን ለማስቀጠል ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል ብለዋል።

በድጋፍ ሰልፉ በነዚህ የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙና ወደ ፊትም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአብሮነትና በወንድማማችነት ለመሻገር ቃል የሚገባበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ሰሞኑን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ስኬቶችን ማስቀጠል ላይ ያተኮሩ ውይይቶች መደረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ሀይሉ፤ በውይይቶቹም ህዝቡ በለውጡ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለ አንስቷል ብለዋል።

በተለይም በወንድማማችነት፣ በአንድነትና በእኩልነት እንዲሁም በአገር ልማት ላይ ለመሳተፍ ለውጡ በር ከፋች እንደነበረ በውይይቱ ላይ በስፋት መነሳቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የክልሉ ሕዝብ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን በመታገል በትብብርና በአንድነት በመነሳት ትኩረቱን በልማትና በሰላም ላይ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሰላማዊ ሰልፉን በተሳካ መንገድ ለማካሄድ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ ማጠናቀቁን በመግለጽ የክልሉ ሕዝብም የሰልፉ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የድጋፍ ሰልፉን ለማስተባበር ወጣቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና የጸጥታ አካላትም አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የድጋፍ ሰልፉ ነገ መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም