በክልሉ እየተካሄደ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው--የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ እየተካሄደ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው--የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ

ሚዛን አማን መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተካሄደ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር አምራቹንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትልና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት የምግብና ሥነ-ምግብ ጉድለትን ለመሙላት የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የማይተካ ሚና አለው።
መርሐ-ግብሩ በግብርናው ዘርፍ የሚታየውን የምርት እጥረት ተከትሎ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት በማረጋጋት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እንደሚያስችል እንደታመነበትም አመልክተዋል።
የክልሉን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በ31 ወረዳዎች በወተት፣ በሥጋና እንቁላል እንዲሁም በማርና በዓሣ ዘርፍ መንደሮችን በመመስረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን ገልጸዋል።
ክልሉ መርሐ ግብሩን ለመተግበር ለእንስሳት እርባታ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን የወተት ተዋጽኦና እንቁላል ምጣኔ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከ500 በላይ የወተት መንደሮች መደራጀታቸውን ገልጸው፤ በእያንዳንዱ መንደር ከ50 እስከ 120 የሚሆኑ የእንስሳት አርቢዎች ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በነፍስ ወከፍ በትንሹ 30 ዶሮ ያላቸው አርብቶ አደሮች በ783 መንደሮች በመርሐ ግብሩ እየተሳተፉ መሆናቸውንም አቶ ታመነ አስረድተዋል።
እንዲሁም 10 እና ከዚያ በላይ የማር ቀፎ ያላቸው የማር አምራቾች በ970 የንብ መንደሮች መደራጀታቸውና ከነዚህም 20ሺህ የሚጠጉ የማር አምራቾች ተለይተው እገዛ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።
ከ400 በላይ በሆኑ መንደሮች በእንስሳት እርባታ እና በከብት ማድለብ ሥራ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በሥጋ አቅርቦት ዘርፍ መሰማራታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በበኩላቸው በዞኑ በመርሐ ግብሩ የአርሶ አደሩን ገቢ በሚያሳድግ መልኩ ትግበራ ውስጥ መገባቱን አስታውቀዋል።
በንቅናቄው በወተት ዘርፍ ያለውን ምርታማነትን ለማሳደግ 1ሺህ 700 በሚሆኑ ጊደሮችና ላሞች ላይ የዝርያ ማሻሻል ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
በዞኑ በስፋት ያልተለመደውን የዓሣ ልማት በመርሐ ግብሩ በማካተት በተደረገው እንቅስቃሴ ከ90 በላይ አነስተኛ ኩሬዎች ተዘጋጅተው ዓሣ እየረባባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን የግብርና ባለሙያ አቶ አክሊሉ አድማሱ በሰጡት አስተያየት በመርሐ ግብሩ የወተትና የሥጋ ምርታማነት እንዲያድግ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት አርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በመርሐ ግብሩ ያለውን ሀብት እንዲያለማ እስከ ታችኛው መዋቅር እየተፈጠረ ያለው ግንዛቤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል።