ኮሌጁ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ሊያሳካ የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ አጁሉ አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ሊያሳካ የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ አጁሉ አሳሰቡ

ጋምቤላ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)፦ የጋምቤላ የመምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ሊያሳካ የሚችል ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ኡሞድ አጁሉ አሳሰቡ።
ኮሌጁ ለሶስት ዓመት በትምህርትና በጤና የሙያ ዘርፎች ያስለጠናቸውን አንድ ሺህ 111 ተማሪዎች ዛሬ በዲፕሎማ አስመርቋል።
የጋምቤላ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ባለፉት ሶስት ዓመታት ክልሉ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ በመካከለኛ ደረጃ የሚፈልገውን የሰው ኃይል በማፍራት በኩል ኮሌጁ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
ኮሌጁ በቀጣይም በዘርፉ የጀመረውን የስልጠና ደረጃ በማሻሻል ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፈራት ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢኮኖሚ ያደጉና የበለጸጉ ሀገራት የመበልጸጋቸው ምስጢር ጠንካራ የትምህርት ፖሊሲና ስልጠና ስርዓት በመዘርጋት በዕውቀት የተገነባ ዜጋ ለመፍጠር በሚያደርጉት የስራ ስምሪት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ኮሌጁ በተለይም አዲስ የተጀመረውን የትምህርት ፓሊሲና ስልጠና ማስተግበር የሚችሉ መምህራን ለማፍራት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ተመራቂዎች በቆይታቸው በተግባርና በንድፈ-ሃሳብ የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ህዝቡን በቅንነት በማገልገል ለሀገር እድገትና ብልጽግና ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የኮሌጁ ዲን አቶ ቾል ኩን በበኩላቸው ኮሌጁ ክልሉ በመካከለኛ ደረጃ በጤናና በትምህርት ዘርፍ የነበረበትን ችግር በማቃለል በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ከዲፕሎማ የስልጠና መረሃ-ግብር በተጨማሪ በዲግሪ ፕሮግራም ስልጠና በመጀመር የሚፈለገውን የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኮሌጁ በዕለቱ ያስመረቃቸው 1ሺህ 111 ተማሪዎች በመምህርነትና በጤና ዘርፍ ለሶስት ዓመታት በመደበኛና በማታው ፕሮግራም ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ብለዋል።
ከተመራቂዎች መካከልም 436ቱ ሴቶች መሆናቸውንም አቶ ቾል ኩን ገልጸዋል።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል እጩ መምህራን ተከተል አቡሌና ታሪኩ ወንደሙ በሰጡት አስተያየት በሰለጠኑበት ሙያ ጠንክረው በመስራት ለትምህርት ጥራት መሻሻል ተግትው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።