ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና በልማት ምክንያት ለተነሱ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ቁልፍ አስረከቡ

101

 

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና በልማት ምክንያት ለተነሱ ዜጎች በዕጣ የመኖሪያ ቤት ቁልፍ ዛሬ አስረክበዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከ150 በላይ አቅመ ደካሞች፣ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞች እና በአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የወንዝ ዳርቻዎችን ለማልማት ለተነሱ 50 አባወራዎች ቤቶቹን ማስረከቡን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።


 

የቤት እድለኞች ከሆኑት ውስጥ በስራቸው ወገኖቻቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ፣ በጤና መጓደል እና በማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የወደቁ እንደሚገኙባቸው ከንቲባ አዳነች ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል “በወንዞች ዳርቻ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በመሆናቸውና በተበከሉ አካባቢዎች መኖር የሚያስከትልባቸውን ችግር ለመፍታት ለዜጎቹ የተሻለና ንጹህ ቤት በመስጠት የአዲስ አበባ ወንዞችን ዳርቻዎች በማልማት ተወዳዳሪና የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

በተጨማሪም “እነዚህን ወገኖቻችንን ከወደቁበት አንስተን ቤት እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር ማአድም አጋርተናል” ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ዕጣ የወጣላቸው ዜጎች ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ እና ባለ ሁለት መኝታ ክፍል ቤቶችን ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም