በአፋር ክልል በመስኖ የለማው የቆላ ስንዴ ምርት እየተሰበሰበ ነው

240


ሰመራ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ሶስት ዞኖች በመስኖ በኩታ ገጠም የለማው የቆላ ስንዴ ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ እንሰሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።


በክልሉ ዘንድሮ 15ሺህ ሄክታር መሬት በሶስት የመስኖ ልማት ክላስተሮች የቆላ ስንዴ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ለኢዜአ ገልጸዋል።


በክልሉ በአዊሲ ረሱ፣ ገቢ ረሱ እና በሀሪ ረሱ ዞኖች  8ሺህ 557 ሄከታር መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በቆላ ስንዴ መስኖ ማልማት እንደተቻለ አስረድተዋል።



አቶ ኢብራሂም  አክለውም በሶስቱም ዞኖች በኩታ ገጠም በመስኖ ለምቶ የደረሰው የስንዴ ሰብል ምርት በአሁኑ ወቅት በኮባይነር እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል። 


በቆላ ስንዴ መስኖ ልማቱ 43 ባለሃብቶች፣ 170 ከፊል አርብቶ አደሮች እና በማህበራት የተደራጁ 330 ወጣቶች ተሳትፈዋል ብለዋል።

 
ከቆላ ስንዴ መስኖ ልማቱ 675ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ አቶ ኢብራሂም ገልጸው ለዕቅዱ ሙሉ በሙሉ አለመተግበር የምርት ማሳደጊያ ግብዓት የአቅርቦት እጥረት ችግር ማጋጠሙን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።



በቀጣይ ለሚካሄደው የቆላ ስንዴ መስኖ ልማት የምርጥ ዘር እጥረት እንዳያጋጥም በ470 ሄክታር መሬት ላይ ከወረር ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ምርጥ ዘር የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። 


በክልሉ አዊሲ ዞን የዱብቲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወል አብዱ  እንዳሉት የቆላ ስንዴን በብዛትና በጥራት አልምተን ከራሳችን አልፈን ለውጭ ገበያ ማቅረብ አለብን የሚል አቋም ተይዞ  በትኩረት እየተሰራ ነው።


በወረዳው በመስኖ የሚለማ ሰፊ ለም መሬት፣ በቂ የውሃ አማራጭና አቅርቦት መኖሩን ገልጸው፤ በልማቱ መሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የወረዳው አስተዳደር ድጋፍና እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።    


 


በመስኖ ልማቱ እየተሳተፉ ካሉት የዓለም ማዕድ አግሮ ግሩፕ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቤተልሄም ኃይሉ እንዳሉት ማህበሩ ስንዴን ጨምሮ የተለያየ ሰብል ለማልማት 304 ሄክታር መሬት ተረክቦ ወደ ስራ ገብቷል። 


በየደረጃው የሚገኘው አመራር ድጋፍ ስላልተለያቸው እስካሁን 75 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ አልምተው ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።


በዚህም 40 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።


አክለውም ቀሪው 200 ሄክታር መሬት በጥጥ ሌላውን ደግሞ በአኩሪ አተር፣ በሰሊጥና በማሾ ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ወይዘሮ ቤተልሄም ተናግረዋል።

 
የአፋር መሬት የሰጡትን የሚያበቅልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም ተባብሮ  በመስራት ከድህነት እንዲወጣም መክረዋል።


ወጣት አባስ ሀሮ በበኩሉ 200 ሄክታር መሬት ተረክቦ እስካሁን 150 ሄክታሩን በስንዴ ማልማቱንና ለ60 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።



በአካባቢው በዓመት ሶስት ጊዜ የተለያየ ሰብል አልምቶ መጠቀም ይቻላል ያለው ወጣት አባስ፤ ወጣቶች በልማቱ ተሳትፈው በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን ችለው ሌሎችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም መክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም