ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሮግራም ከ630 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሮግራም ከ630 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጸደቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015(ኢዜአ)፦ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሮግራም ከ630 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማጽደቁን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የፋውንዴሽኑ ፕሬዝዳንት ሪታ ሮይና ሌሎች የስራ አመራር ቦርድ አባላት ባለፉት አራት ቀናት በኢትዮጵያ የፕሮግራም ግምገማ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት ለሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሮግራም ከ630 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማጽደቁን ሚኒስትሯ አመልክተዋል።
የጸደቀው ገንዘብ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የብድር አገልግሎት ለማቅረብ፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በስራ ፈጣሪነት አስተሳሰብ ለመቅረጽ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ገንዘቡ ለስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለተለያዩ ተግባራት ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚውል ነው ብለዋል።
ፋውንዴሽኑ አካታችና ፍትሐዊ ዓለም ለመፍጠር፣ ትምህርትን ለማስፋፋት፣ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርና የፋይናንስ አካታችነትን የማስተዋወቅ ተልዕኮ ያለው መሆኑን ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት።
ከፋውንዴሽኑ የቦርድ አመራሮች ጋር በርካታ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም ፋውንዴሽኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ያከናወናቸውን ተግባራትና የተጫወተው ሚና ላይ ዝርዝር ምልከታ መደረጉን ሚኒስትሯ ልጸዋል።