ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ወደ ውድድር ይመለሳሉ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2015 (ኢዜአ)፦ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

ፕሪሚየር ሊጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ ባደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ለሶስት ሳምንት ተቋርጦ ነበር።

ውድድሩ በ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብር ሲመለስ መቻል ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መቻል በ23 ነጥብ 5ኛ እንዲሁም አዳማ ከተማ በ21 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ሲዳማ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና ከምሽቱ 12 ሰአት ይጫወታሉ።


 

ሲዳማ ቡና በ19 ነጥብ 13ኛ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና በ21 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ፋሲል ከነማ ከወላይታ ዲቻ ከቀኑ 9 ሰአት እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ከምሽቱ 12 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ተስተካካይ መርሐ-ግብሩ እስከ መጋቢት 26/2015 ይቆያል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በድሬዳዋ ስታዲየም ለማካሄድ ቀን ተቆርጦለት ነበር።

በድሬዳዋ ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ ሜዳው በመበላሸቱና በቀላሉ ሊያገግም ባለመቻሉ አንድ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታ ከተካሄደ በኋላ አወዳዳሪው አካል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማየት ቀሪ የከተማው የመጨረሻ ጨዋታዎች መሰረዛቸውን ማሳወቁ የሚታወስ ነው።

የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ውሳኔውን ተከትሎ በባህርዳር፣ አዳማና ሐዋሳ ከተሞች ያሉ ስታዲየሞች ፕሪሚየር ሊጉን ለማጫወት ያላቸውን ዝግጁነት መገምገሙ አይዘነጋም።

በዚሁ መሰረት ከ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች እስከ 27ኛ ሳምንት ውድድሩ በቅደም ተከተል በመጀመሪያ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየምና በቀጣይ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንዲካሄዱ አክሲዮን ማህበሩ መወሰኑ ይታወቃል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ35 ነጥብ ይመራል።

ባህር ዳር ከተማና ኢትዮጵያ መድን በተመሳሳይ 30 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አርባ ምንጭ ከተማ፣ኢትዮ ኤሌትሪክና ለገጣፎ ለገዳዲ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም