የነዳጅ ግብይትን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት የመፈጸም አሰራር በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ጀመረ

697

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2015(ኢዜአ) የነዳጅ ግብይትን በዲጂታል የክፍያ ስርዓት የመፈጸም አሰራር በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ተግባራዊ መሆን ጀመረ፡፡

የዲጂታል ክፍያው ትግበራ የተጀመረው በነዳጅ ድጎማ ስርዓት ተጠቃሚ የሆኑትን ጨምሮ በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ መሆኑም ተገልጿል።

የክፍያ ስርዓቱን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፣የኢትዮጰያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ እና  የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በይፋ አስጀምረዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ የነዳጅ ግብይት ስርዓት መዘመን ለትራንስፖርት አገልግሎት መሳለጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በተጨማሪም ከነዳጅ አቅርቦት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ህገ-ወጥነትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ይህ አገልግሎት በአጭር ግዜ ውስጥ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚሆን  ጠቁመዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገባቸው ግብዓቶች ውስጥ ነዳጅ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይሁንና  የነዳጅ አጠቃቀምና ስርጭት እንደ አገር ክፍተቶች ያሉበት ከመሆኑ ባሻገር ፍትሃዊ ተደራሽነት ላይም ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ግብይቱ ለህገ-ወጥነት ተጋላጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የዲጂታል ግብይት ስርዓቱ በዘርፉ የሚነሱ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ከተጀመረ ስምንት ወራትን ማስቆጠሩን አስታውሰዋል።


 

በድጎማ ስርዓቱ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎችም የነዳጅ ግብይታቸውን በቴሌ-ብር እንዲፈጽሙ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህንን መነሻ በማድረግ ለሁሉም ተሽከርካሪዎች የዲጂታል የነዳጀ ግብይት ስርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት።

መንግስት ለነዳጅ ብቻ በዓመት ከ4 ቢሊዬን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚያወጣ ገልጸው ግብይቱ ወደ ዲጂታል መደረጉ ለቁጥጥር ስርዓቱ የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ  ፍሬህይወት ታምሩ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ረገድ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በተለይም በተለያዩ ዘርፎች የቴሌ-ብር ግብይት መፈጸም መጀመሩ የዜጎችን ኑሮ ከማቃለሉ ባሻገር የገንዘብ ዝውውሩ ከእጅ ንኪኪ የጸዳና እንዲሆን አስችሏል።

ዛሬ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ይህ የዲጂታል የነዳጅ ግብይት ስርዓትም ዲጂታል ኢኮኖሚን በማረጋገጥ ረገድ ፈር ቀዳጀ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።

ለዚህም አገልግሎቱ ሳይቆራረጥ በቀላሉ የሚሰጥበት አማራጮችን በማስፋት ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ።

በቴሌ ብር አማካኝነት የሚከናወነው የታለመለት የነዳጅ ድጎማም የቁጥጥር ስርዓቱን እንዳሻሻለው ጠቁመዋል፡፡

ዲጂታል የነዳጅ ግብይቱን ከቴሌ ብር በተጨማሪ በሌሎች የዲጂታል አማራጮችን ለማስፋት ከባንኮች ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተነስቷል። 

 

 

 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም