ታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የመገባደጃ ምዕራፍ ላይ ደርሷል -- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

381

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2015(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ የመገባደጃ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን የሚመሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የግድቡ ግንባታ አፈፃፀምና የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት በዓል አከባበር በተመለከተ ምክክር አድርጓል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያዊያን ያለ ልዩነት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ 18 ቢሊዮን ብር በተለያዩ መንገዶች መሰብሰቡን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያንና ፕሮጀክቱን የሚመሩ አካላት ለትውልድ የሚሸጋገር የሚያኮራ ስራ አከናውነዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ላለፉት 12 ዓመታት በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በእውቀትና በሌሎች አግባቦች አስተዋጽኦ በማድረግ ግንባታው በመገባደጃ ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ይሀም "ኢትዮጵያውያን ስናብር ምን ያህል አቅም እንዳለን የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር በተግባር በሚለካ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ መሳታፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድርጋይ የተቀመጠበትን በዓል ስናከብር በዲፕሎማሲው መስክ የተጀመሩ ውጤቶችንም ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።፡

ኢትዮጵያ የተጀመረው የሶስትዮች ድርድር በአፍሪካ ማዕቀፍ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ አንድን አካል ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ የኋልዮሽ አካሄድ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡


 

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ሲያበረክቱት የነበረው አስተዋጽኦ "ትውልድ የሚያኮራ የነገ ታሪክ ነው" ብለዋል፡፡

በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ የሚያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡


 

የግድቡ ግንባታ አሁን የደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና የፈጸመችው ታሪካዊ ድል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስቴር ተስፋዬ በልጂጌ ናቸው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ ቀጣናውን በኃይል የሚያስተሳስር የአፍሪካውያን ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም