የሚቀረጸው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጭ አገርን ከግጭት አዙሪት አውጥቶ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ያስችላል - ፍትህ ሚኒስቴር

501

ሚዛን አማን መጋቢት 22/2015  (ኢዜአ) አዲስ የሚቀረጸው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጭ አገርን ከግጭት አዙሪት በማውጣት አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት እንደሚያስችል የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዓለምአንተ  አግደው በሚዛን አማን አተማ እየተካሄደ ባለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉባዔ ላይ እንዳመለከቱት፣ መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አገራዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ እየሰራ ነው። 

የቆዩ በደሎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎችን በተጠያቂነት እንዲሁም በዕርቅና በይቅርታ በመዝጋት ከግጭት አዙሪት ወጥቶ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት አዲስ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ለመቅረጽ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

ለዚህም የፖሊሲ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ለሽግግር ፍትህ መሳካት ሁሉም  አካላት ርብርብ እንዲያደረጉ ጠይቀዋል።

ከለውጡ ማግስት ከሀገር ውስጥና ከውጭ የገጠሙን ፈተናዎች ብዙ ዋጋ እንዳስከፈሉ የገለጹት አቶ ዓለምአንተ፣ "በሰሜኑ የነበረው ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱ ብስለት የተሞላበትና የአመራር ጥበብ የታየበት" ነው ብለዋል።

"ስምምነቱ ኢትዮጵያን አሸናፊ ከማድረግ ባሻገር ታሪካዊ ጠላቶችን አንገት ያስደፋና እኩይ ዓላማቸውን ያመከነ ነው" ብለዋል። 

መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና ሙስናን  ለመታገል በቁርጠኝነት የጀመራቸው ስራዎች  ውጤታማ እንዲሆኑ መረባረብ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። 

"ወሳኝ የአገር ግንባታ ምዕራፍ ውስጥ በመሆናችን ለለውጡ ስኬትና አገራዊ ወንድማማችነት መጎልበት በትኩረት መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራዎችን ለመደገፍና ለማጠናከር ሁሉም ትኩረት እንዲሰጥም አቶ ዓለምአንተ ጠይቀዋል።

በተለይ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ፣ ግጭቶች በዘላቂነት ተፈትተው ሰላምን ለማስፈንና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት እንዲጠናከር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የጎላ ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅማ ዲልቦ በበኩላቸው፣ "እንደ አገር ያጋጠሙ ስብራቶችና ያልተሻገርናቸው ፈተናዎችን ለማስወገድ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አገራዊ ጉዳዮች ላይ በአዎንታዊ ጎን ተረባርበው እንዲሰሩ ማስቻል የባለሥልጣኑ የሁልጊዜ ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል።

አገራዊ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ሆነ ያልተሻገርናቸውን ፈተናዎች በድል ለማለፍ ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጎች በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ፍትህ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጮችን ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን በአዲስ አበባ እና በክልሎች እያካሄደ ስለመሆኑ በቅርቡ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም