የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሕዝብና መንግስትን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መረጃን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል- ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ 

629

አዲስ አበባ (ኢዜአ)  መጋቢት 22/2015 የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሕዝብና መንግስት ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መረጃን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በጋራ በመሆን ከፌደራል ተቋማት ለተወጣጡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሲሰጡት የነበረው ስልጠና ተጠናቋል፡፡ 

በማጠናቀቂያ መርሐግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ፤ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችም ትክክለኛ መረጃን ለዜጎች ተደራሽ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡  

ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑ መረጃዎች ደግሞ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የማያውኩ፣ የወጣቶችን ጤና የማይጎዱና ዜጎችን ለግጭት የማይዳርጉ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡  


 

በመሆኑም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሕዝብና መንግስት ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መረጃን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል  ብለዋል፡፡፡  

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት ዶክተር እንዳለ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጸሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው  ተቋማቸውን በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ 


 

ኢዜአ ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ተቋማት መሰል ስልጠና መስጠቱን ጠቅሰው፤በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡  

ሰልጣኞቹ በቀጣይ ያገኙትን ክህሎት ይበልጥ ለማዳበር ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በስልጠናው የተሳተፉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በበኩላቸው በስልጠናው የተሻለ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም ቀጣይም እውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም