በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው መሬት ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ ተሰብስቧል

495

ባህር ዳር  መጋቢት 22 /2015 (ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወቅት  በመስኖ  ከለማው የስንዴ ማሳ  ከ20 ሺህ ሄክታር  በላይ ምርት   መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ዋገጠራ ቀበሌ በመስኖ የለማ  የስንዴ ማሳ በመስክ ተጎብኝቷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በወቅቱ እንደገለጹት፤ የምግብ ዋስትናን  ለማረጋገጥ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረ ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በዚህም በዘንድሮው የበጋው ወቅት  ከ213 ሺህ ሄክታር በላይ  በስንዴ ከለማው መሬት  ውስጥ ከ20 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

በክልሉ በመስኖ ስንዴ ልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙ ከ700 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ካለሙ የስንዴ ምርት በሄክታር በአማካኝ 40 ኩንታል ምርት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞንም በበጋ ወራት በመስኖ ስንዴ እንዲያለማ ከተሰጠው ዕቅድ በላይ በማልማት ውጤታማ የሆነ ተግባር በማከናወኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። 

የለማውን የስንዴ ምርትም ብክነት በሚቀንስ መልኩ እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም እየናረ ያለውን የገበያ ዋጋ ከማረጋጋት ባለፈ የዱቄት ፋብሪካዎችን የግብዓት እጥረት ለማቃለል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በቀጣይ ከዘንድሮው የበለጠ መሬት በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ  ሁሉም የጀመረውን ቅንጅታዊ ስራ  አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሮ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ የነበረውን የአመለካከት ችግር በማቃለል   22 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት  ዘንድሮ ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል።

ከድህነት መሻገር የምንችለው ያለንን ዕምቅ የውሃ ሃብትና መሬት አቀናጅተን በውጤታማነት ማልማት ስንችል ነው ያሉት አቶ ይርጋ ለዚህም የክልሉ አመራር ትኩረት ሰጥቶ እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀጣዩ ዓመት 50 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማም ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረጉን የገለጹት በደቡብ ጎንደር ዞን የዋገጠራ ቀበሌ አርሶ አደር አዱኛ አላምር ናቸው።

በሩብ ሄክታር መሬት ካለሙት የመስኖ ስንዴ 6 ኩንታል ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል መሬቱን በበጋ ወራት ጓያና ሽንብራ ሲዘሩ ከአንድ ኩንታል ተኩል ያልበለጠ ምርት ያገኙበት እንደነበር አስታውሰዋል።

የዚሁ ቀበሌ  አርሶ አደር መኮንን አዲስ፤   የጀመሩት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከድህነት ሊያወጣቸው እንደሚችል ተስፋ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም የበጋ ስንዴ ልማቱን አጠናክረው   የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን  እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል  ባለፈው ዓመት የበጋ ወቅት በመስኖ  ከለማው 40 ሺህ ሄክታር መሬት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ  ምርት መሰብሰብ መቻሉን በወቅቱ ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም