በኢትዮጵያ በግጭት ውስጥ የነበሩ ቡድኖችን ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ እየተሰራ ነው

368

ባህር ዳር መጋቢት 22/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በግጭት ውስጥ የነበሩ ቡድኖችን ወደ ሰላማዊ ህይወት በመመለስ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።

ኮሚሽኑ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የምክክር መድረክ  አካሂዷል።

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ መድረኩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ የመተማመን ፖለቲካ ለማስፈን መንግስት የተለያዩ ኮሚሽኖችን አቋቁሞ እየሰራ ነው።

በእዚህም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነትና በግጭቶች ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም፣ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስና ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኮሚሽኑም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የተሳተፉ ተዋጊ ቡድኖችን ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

"በእዚሀም ግንዛቤ በመፍጠር ቡድኖቹ ትጥቅ ፈትተው የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲወስዱና በሚፈልጉት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ይሰራል" ብለዋል።

ይህም ለአገር ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ባለድርሻ አካላት በቀና ልብ እንዲተግብሩት አምባሳደር ተሾመ ጠይቀዋል።

"በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶችና የሰላም እጦት ምክንያት በህዝቡ ላይ ስጋት እንዳለ እንገነዘባለን" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ይሄን ስጋት ለመቀነስ በሁሉም አካባቢዎች ትጥቅ የማስፈታት ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

"በዚህም ከመደበኛ የፀጥታ ተቋማት ውጭ ያሉ ቡድኖችን ትጥቅን በማስፈታት ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ፣ ችግር ቢፈጠር እንኳ በክልል ፖሊስና በፌደራል የፀጥታ ሃይሎች መቆጣጠር የመንግስት ሃላፊነት ይሆናል" ብለዋል።

አምባሳደር ተሾመ እንዳሉት በመልሶ ማቋቋም ሥራው የቀድሞ ተዋጊዎች፣ ጉዳት የደረሰባቸው አረጋውያን፣ የተዋጊ ልጆች የሚካተቱ ይሆናል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በክልሉ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ማስከተሉን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር ናቸው።

ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ በተሰጠው ሃላፊነት ቡድኖችን ትጥቅ ከማስፈታት ሥራ ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ዜጎችን የሰላም ተስፋ ለማለምለም መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

በዚህም የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት፣ የተፈናቀሉትን በማቋቋምና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን በማከናወን ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ሰርተው የሚኖሩበትና የሚለወጡበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ባለስልጣናት፣ የኮሚሽኑ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም