የዓባይ ተፋሰስን ደህንነት በዘላቂነት ለመጠበቅ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

ባህር ዳር መጋቢት 22/2015 (ኢዜአ)  የዓባይ ተፋሰስን ደህንነት በዘላቂነት ለመጠበቅና የሕዳሴውን ግድብ ከደለል ለመታደግ ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሀም አዱኛ ገለጹ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እና የጣናን ሐይቅ ደህንነት መጠበቅ በሚቻልበት ላይ ያተኮረና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አውደጥናት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በአውደ ጥናቱ ላይ እንዳሉት፣ ሚኒስቴሩ የዓባይ ተፋሰስ የውሃ አስተዳደርን በአዲስ በማዋቀር የሪፎርም ሥራ እየሰራ ይገኛል።

"አገሪቱ በርካታ የውሃ ሃብት ቢኖራትም የውሃ ሃብት አያያዝና ደህንነትን በዘላቂነት መፍታት ባለመቻሉ በአንድ በኩል የውሃ አቅርቦት በሌላ በኩል የጎርፍ መጥለቅለቅ ችግር እየተከሰተ ይገኛል" ብለዋል።

ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት የተሳተፉበት ጥናት በአሁኑ ወቅት መጠናቀቁን ዶክተር አብርሀም ገልፀዋል።

የዓባይ ተፋሰስ ሲታሰብ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ጣና ሐይቅ እና ሌሎች የዓባይ ተፋሰሶችን ደህንነት መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዓባይ ተፋሰስን ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅና ግድቡን ከደለል ለመታደግ በመንግስት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

"የዓባይ ተፋሰስ በቆዳ ሽፋን የአገሪቱን 20 በመቶ፣ ከአገሪቱ የህዝብ ቁጥር 30 በመቶ፣ ከሃገሪቱ የውሃ ሃብት 45 በመቶ ይሸፍናል" ያሉት ደግሞ የዓባይ ተፋሰስ አስተዳደር ቢሮ ዋና ሃላፊ አቶ የወንድወሰን መንግስቱ ናቸው።

ከተፋሰሱ ውስጥ ጣና ሐይቅ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሰፊውን ቦታ እንደሚይዙ ጠቁመው፤ "የተፋሰሱ አካባቢ ለእርሻ፣ ለእንስሳት እርባታና ለዓሣ ማስገር ሥራ በመዋሉ ለጉዳት እየተጋለጠ ይገኛል" ብለዋል።

በተፋሰሱ ዙሪያ በተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ክፍተት በመኖሩ ቦታው ለተፈጥሮ ሃብት መራቆት መዳረጉን የገለጹት ሃላፊው፣ "ይህም ጣናን ጨምሮ ተፋሰሶች በደለልና በሌሎች በካይ ኬሚካሎች እንዲሞሉ እያደረገ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም በተፋሰሱ ዙሪያ ለመጠቀም በሚደረገው ግብግብ ልክ ለደህንነቱ መጠበቅም ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

እንደ ዓባይ ተፋሰስ አስተዳደር ቢሮ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ  እቅድ ተነድፎ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን የጣና ሐይቅን ከደለል መሞላት ለመታደግ በገባር ወንዞች አካባቢ የችግኝ ተከላ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በጣና ሐይቅ ተግዳሮቶች ዙሪያ መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የዓባይ ተፋሰስ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ አቶ አህመድ ታደለ እንዳሉት፣ ለጣና ሐይቅ ተግዳሮት ዋነኛ ምክንያት በየአካባቢው ያሉ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን መወጣት አለመቻል ነው።

በጣና ሐይቅ ዙሪያ የሚኖረው ህዝብ የተፈጥሮ ሃብት ያላግባብ እንዲመናመን ማድረጉ ለአፈር መሸርሸርና ጣና በደለል እንዲሞላ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

"ችግሩን ለመፍታት በየአካባቢው ህብረተሰቡን በማስተማር ግንዛቤውን ከማሳደግ ባለፈ ለሐይቁ ዘላቂ ደህንነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የዘርፉ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም