በኢትዮጵያ የእንሰሳት ሀብት ምርታማነትን ለማሳደግ ለእንሰሳት ጤና ትኩረት ተሰጥቷል - የግብርና ሚኒስቴር

136

አዳማ መጋቢት 22 /2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የእንሰሳት ሀብት ምርታማነትን ለማሳደግ ለእንሰሳት ጤና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ 11ኛውን ሀገር አቀፍ የበጎችና ፍየሎች ደስታ መሰል በሽታ ላይ ያተኮረ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል።


 

የግብርና የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶክተር ዮሐንስ ግርማ ከእንስሳት ሀብት ከፍተኛ የስጋ፣ የወተትና የወተት ተዋፅዖ ምርት ለማግኘት ከዝርያ ማሻሻልና መኖ ልማት ባሻገር በእንስሳት ጤና ክብካቤና አጠባበቅ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይ አሁን ወደ ትግበራ የገባውን የሌማት ትሩፋት መርሐግብር ለማሳካት በሽታን ከመከላከልን ጨምሮ በእንስሳት ሀብት ጤና አጠባበቅና ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የበጎችና ፍየሎች ደስታ መሰል በሽታዎችን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታን የመቆጣጠርና የማጥፋት ስራ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በጎችና ፍየሎችን ጨምሮ የእንስሳት ሀብት ጤናን በመጠበቅ በቂ የስጋና የወተት ምርት እንዲኖር የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2027 ደስታ መሰል የበጎችና ፍየሎች በሽታን ለማጥፋት መታቀዱንም ነው ዶክተር ዮሐንስ የጠቆሙት።

ደስታ መሰል በሽታን ከአገር ለማጥፋት የተቀመጠውን ግብ እውን ለማድረግ ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ሴክተር ተቋማት መረባረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የበጎችና ፍየሎች ደስታ መሰል በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ዘመቻ አስተባባሪ ዶክተር ሜሮን ሞጎስ በበኩላቸው በሽታውን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት እየተደረገ ባለው ጥረት ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ54 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ በጎችና ፍየሎች ክትባት መሰጠቱን ገልጸዋል።


 

በተጠቀሱት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይም በአፋር፣ሶማሌ፣ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በሽታውን ለማጥፋት የቅንጅት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የደስታ መሰል የበጎችና ፍየሎች በሽታን ጨምሮ ሌሎች የእንስሳት በሽታ ምልክቶችን በመከታተል ፈጣን የክትባት አገልግሎት በመስጠት ረገድ ውጤታማ ስራ መሰራቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም