የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ  የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሊያከበር ነው 

531

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2015 (ኢዜአ):-የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የተመሰረተበትን  100ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚያክብር አስታወቀ።

ሜዲካል ኮሌጅ የተመሰረተበተን 100ኛ ዓመት አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የተመሠረተው በ1915 ዓ.ም ነው።

መስራቹ ሲዊድናዊ ሀኪም ዶክተር አይነር ሲሆኑ እስከ 1928 ዓ.ም በሜዲካል ዳይሬክተርነት ያገለገሉ ሲሆን የተቋሙ የመጀመሪያ የመጠሪያ ስም ቤተሳይዳ በተፈሪ መኮንን ይባል ነበር።

በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር የተቋሙን መጠሪያ ወደ ባቶሪያ በመለወጥና አዲስ ህንፃ በማስገንባት አገልግሎት የሰጠ ሲሆን በ1967 ዓ.ም ደግሞ የካቲት 12 ሆስፒታል በመባል ተቀየረ።

በ2003 ዓ.ም ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በማደግ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኘ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ኘሮቮስት ዶክተር ኤልያስ ተዋበ እንዳሉት ኮሌጁ በ100 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት እያሻሻለ መጥቷል።

ሆስፒታሉ በእነዚህ ዓመታት በተመላላሽ፣ በተኝቶ ማከምና ድንገተኛ ህክምና እየሰጠ ሲሆን የኤክስሬይ ምርመራ፣ የነርሲንግ ህክምና ትምህርትና የደም ልገሳን በቀደምትነት ያስተዋወቀ ሆስፒታል መሆኑንም ገልጸዋል።

ተቋሙ በቀዶ ጥገና ከአንገት በላይ ህክምና ጨምሮ የጉበትና የኩላሊት፣ የሽንት ቱቦ ህክምና፣ የአንጎልና ህብለሰርና ምርመራን ጨምሮ ሌሎች ህክምናዎችን እየሰጠ ነው።

በተለይ የቃጠሎና የከንፈር ላንቃ ክፍተት ህክምና ከሌሎች ሆስፒታሎች በተለይ ለበርካታ ህሙማን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የስፔሻሊስት ሀኪሞች ብዛትና ጥራት ለማሻሻል በህጻናት ህክምና፣ በውስጥ ደዌ ፣ በጠቅላላ ቀዶ ጥገና ፣በማህጸን ጽንስ ስፔሻሊስት፣ በአፍና መንጋጋ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት በሰመመንና ጽኑ ህሙማን ህክምና እያሰለጠነ ነው ብለዋል።

እነዚህ ባለሙያዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ተቋም የመምራትና ችግር ፈቺና የጤና መረጃ አያያዝ ለማሻሻልና ለማዘመን የሚያስችል አቅም ያላቸው ባለሙያዎች የሚፈሩበት መሆኑን ነው የተናገሩት።


 

የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ኘሮቮስት አቶ አለሙ ክብረት ከህክምና በተጨማሪ የባለሙያን ችግር ለመፍታት በተመረጡ ዘርፎች ትምህርት እየሰጠና በርካታ ባለሙያዎች እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሜዲካል ኮሌጁ ባለሙያዎች በማፍራት በኩል የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ ሲጀምር ከነበሩት 25 ያልበለጡ አልጋዎች አሁን ላይ የአልጋዎችን ቁጥር ወደ 700 ያሳደገ መሆኑንና 39 የሚሆኑ የህክምና አይነቶች እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

100ኛ ዓመቱንም በዚህ ዓመት ሲያክብር የነጻ ህክምናን ጨምሮ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ህሙማንም በርካታ ባለሙያዎች በማሳተፍ በዘመቻ መልክ ህክምና ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ የየካቲት 12 ሜዳካል ኮሌጅ የጤና ስርዓቱን በማዘመን ህክምና በመስጠት እያደረገ ያለው ተግባር በአርያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

100ኛ ዓመቱን በማስመልከት በሚያደርገው በጎ ተግባር የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም