ከአዲስ አበባ ስምንት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ከአንድ ሺህ በላይ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
ከአዲስ አበባ ስምንት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ከአንድ ሺህ በላይ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ተመረቁ

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2015 (ኢዜአ):- በአዲስ አበባ በሚገኙ ስምንት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ 1 ሺህ 136 ከስደት ተመላሽ ዜጎችና በኢትዮጵያ የተጠለሉ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ተመረቁ።
ለስድስት ወራት በአውቶ መካኒክ፣ኤሌትሪክሲቲ፣ልብስ ስፌት፣ጨርቃ ጨርቃና ሌሎች መስኮች ስልጠና መውሰዳቸው ተመላክቷል።
የስልጠናው በጀት የተሸፈነው በመንግስትና በጀርመን ተራድኦ ልማት ድርጅት ድጋፍ መሆኑ ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩባትም ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ ግልፅ ፖሊሲ አውጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ምርቃቱም የዚሁ ፖሊሲ አካል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በቢሮው ስር የሚገኙ 14 ኮሌጆች በ124 የሙያ መስኮች ሌሎች ወጣቶች በመሰልጠን ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ስደተኞች በቆይታቸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም ሊጠቅም የሚችል የሙያ ክህሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በተለያዩ መስኮች ሰልጥነው ብቁ መሆን እንዲችሉ በኢትዮጵያ መንግስት ለተደረገላቸው መልካም ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።