የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን ከመንግስት የልማት ፖሊሲዎች ጋር ማስተሳሰር አለባቸው--ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

181

ሚዛን አማንመጋቢት 22/2015 (ኢዜአ) ፡-የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን ከአገራዊ ነባራዊ ሁኔታና ከመንግስት የልማት ፖሊሲዎች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስታወቁ።

የፌዴራል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከክልልና ፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር ሰባተኛውን የጋራ የምክክር ጉባኤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በምክክር መድረኩ ላይ ላይ እንደተናገሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመንግሥት በጀት በማይደርስባቸው የልማት ተግባራት ላይ በመሰማራት እየደገፉ ነው።

ድርጅቶቹ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ለአገር ግንባታ ተጨማሪ አቅም ስለሚሆኑ ለውጤታማነታቸው ከመንግሥት የልማት ፖሊሲ ጋር ማጣጣም እንደሚገባ ገልጸዋል።

"ድርጅቶቹ የሚያገለግሉት ህብረተሰቡን በመሆኑ ሥራዎቻቸውን በቅርበት መደገፍና ክትትል ማድረግ ይገባል" ሲሉም ጠቁመዋል።

በክልሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ድርጅቶቹ ተደራሽነታቸውን እንዲያስፋፉ ጠይቀዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

"በእዚህም ድርጅቶቹ የአገር ግንባታ ሂደቱን ተገንዝበው እንዲያግዙ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

ድርጅቶቹ እስካሁን ካበረከቱት አስተዋጽኦ በላቀ ትጋትና ትርጉም ባለው መልኩ በመስራት አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲጫወቱም ሚኒስትር ዴኤታው ጠይቀዋል።

የፌዴራል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአገሪቱን ሕግና ሥርዓት አክብረው በመንቀሳቀስ ለአገራዊ ለውጥ ጉዞ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህንን እውን ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንና ባለስልጣኑ ከክልልና ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ስምምነት ተፈራርሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ድርጅቶቹ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የኢኮኖሚ ተዋናይ የሚሆኑበትና በአገራዊ ጉዳዮች ተቀራርበው የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው ጉባኤ የሁሉም ክልሎችና የፌደራል ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም